የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ደህንነት አስተማማኝ አይደለም በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው - የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ደህንነት አስተማማኝ አይደለም በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው - የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን
አዲስ አበባ ነሀሴ 27/2010 የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ቁጥጥር ደህንነት አስተማማኝ እንዳልሆነ በመግለፅ የኬንያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ያሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ገለፀ። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሰራተኞች የደመዋዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጥያቄን በማቅረብ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል። የሥራ ማቆም አድማውን ተከትሎ የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በተለይ ወደ ኬንያ ለሚያቀኑ በረራዎች እየሰጡ ያለው መረጃ የተሳሳተ ነው የሚል መግለጫ አውጥቷል። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ግን ማህበሩ ያሰራጨው ይህ መግለጫ "ተቀባይነት የሌለው፣ ሀሰተኛና ከሙያው ስነ-ምግባር ያፈነገጠ ነው" ሲል ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስተባብሏል። ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት የአየር ትራፊክ መቆጣጠር ተግባሩን የሚያከናውነው ለሥራው የሚፈለገውን ደረጃ በሚያሟሉና ተገቢውን ስልጠና በወሰዱ ባለሙያዎች መሆኑን በመግለጫው ጠቅሷል። በዚህ ረገድም ከየትኛውም ወገን ምንም አይነት ቅሬታ የሌለና የአየር መንገዱ በረራዎች ያለምንም ችግር እየተከናወኑ መሆናቸውን አትቷል። ይህንንም መላው ህብረተሰቡ፣ አየር መንገዶች፣ የአገር ውስጥና የአለም አቀፍ ተቋማት ሊያውቁት ይገባል ሲልም አመልክቷል። ይሁንና የኬንያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ችግር እንዳለ አስመስሎ የሚያናፍሰው ሀሰተኛ ወሬ ተቀባይነት የሌለውና ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያልተከተለ ነው ሲልም ወቅሷል። ማህበሩ የሚያደርገው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤትን ስምና ዝና የሚጎዳ መሆኑ ታውቆ የኬንያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ባለስልጣን በማህበሩ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በመግለጫው ተጠይቋል። ባለስልጣኑ በማህበሩ ላይ ተገቢውን እርምጃ የማይወስድ ከሆነ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጉዳዩን ወደሚመለከተው አለም አቀፍ አካል ለማቅረብ እንደሚገደድም ገልጿል። በአሁኑ ወቅት በሥራ ማቆም አድማው ላይ የተሳተፉ አንዳንድ ሰራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እየተመለሱ ሲሆን የባለስልጣኑ እንቅስቃሴም በተገቢው ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ተጠቁሟል።