ኢንስቲትዩቱ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ የካቲት 24/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ኢንስቲትዩቱ ካደረገው ድጋፍ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን 120 ሺህ ብር ግምት ያለው ደግሞ የቁሳቁስ ድጋፍ መሆኑ ታውቋል።
ድጋፉን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ፤ የተደረገው ድጋፍ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም ተመሣሣይ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ወገኖቻችንን ለማገዝ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ፤ ኢንስቲትዩቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎችም ተመሳሳይ ድግፍ በማድረግ ለወገን ደራሽ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።