አርሶ አደሩ የግብርና ምርታማነቱን ከእጥፍ በላይ እንዲያሳድግ ለመደገፍ መንግስት ይሰራል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሩ የግብርና ምርታማነቱን ከእጥፍ በላይ እንዲያሳድግ ለመደገፍ መንግስት ይሰራል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ
ባህር ዳር ፤ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) አርሶ አደሩ የግብርና ምርታማነቱን ከእጥፍ በላይ እንዲያሳድግ በቴክኖሎጂና ግብዓት ለመደገፍ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በተገኙበት "የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አስተዋጽኦ ተኪ የሆነ ተወዳዳሪ የለውም'' በሚል ርዕሰ ጉዳይ የምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
ርዕስ መስተዳደሩ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የግብርና አስተራረስ ዘዴ ረጅም ዘመን ቢያስቆጥርም ከልማዳዊ አስተራረስ ያልተላቀቀ ነው።
"ዘርፉ በቴክኖሎጂ ተደግፎ እድገትን በዘላቂነት ማስመዝገብ ባለመቻሉም አሁን ድረስ በቤተሰብ ደረጃ በምግብ እህል አቅርቦት እራስን መቻል አልተቻለም" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የቆላ ስንዴ አስተራረስ ዘዴ ተስፋ ሰጭ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ይህንን ማስፋት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ እራስን የመቻል እድሉ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ ተቋማት፣ የባለሃብቶች፣ የመንግስት እና የምሁራን ቅንጅትና በትብብር መስራት ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ከማቅረብ በተጨማሪ እንደ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ያሉ የግብርና ግብአቶችን አብሮ በማቅረብ ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ እንደሚቻልም ዶክተር ይልቃል አስረድተዋል።
ለዚህም መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ አርሶ አደሩ በዩኔዬኖች ታግዞና በጋራ በመሆን ቴክኖሎጂዎችን ገዝቶ የሚጠቀምበትን ዕድል ማመቻቸትና ማበረታታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን ከተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም የባንክ ሥራ አስኪያጆች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እየተሳተፉ ይገኛል።
ከምክክሩ በኋላ በባህር ዳር ከተማ ዘንዘልማ ቀበሌ በመስኖ የለማ የስንዴ ሰብል ይጎበኛል፡፡