ቀጥታ፡

በኢትዮጵያዊያን ጀግንነት በደማቅ ታሪክ የታተመውን የአድዋ ድል ስናከብር እኛም ሌላ ድል ለማስመዝገብ በመዘጋጀት መሆን አለበት

የካቲት 23/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ተጋድሎ በደማቅ ታሪክ የታተመውን የአድዋ ድል ስናከብር እኛም ሌላ ድል ለማስመዝገብ በጋራ በመስራት መሆን አለበት ሲሉ በአዲስ አበባ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ።
126ኛው የአድዋ ድል በዓል ‘’አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት የአፍሪካዊያን የነፃነት ጮራ’’ በሚል መሪ ቃል በብሄራዊ ደረጃ ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በአደባባዮች ተገኝቶ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ አክብሮታል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ ኢትዮጵያ እንደ አድዋው ድል አድራጊዎች ሁሉ አሁን ላይ ድህነትን ታግለው የሚያሸንፉ ጀግኖችን ትሻለች ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከኋላ ቀርነት፣ ድህነት፣ ችግርና ሰቆቃ ለማላቀቅ በልዩነቶች ላይ አተኩሮ ከመከፋፈል ይልቅ በጋራ ቆመን አገር የምናለማበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባት የሆኑት ሊቀ አበባው አድባር ተገኝ፤ የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ የነፃነት ትግል መጠናከር አዲስ ምዕራፍ የከፈቱበት ታሪካዊ እለት በመሆኑ ለማክበር ተገኝቻለሁ ብለዋል።

በመሆኑንም በቀደሙት የኢትዮጵያ ጀግኖች የትግል ውጤት በደማቁ የታተመውን የአድዋ ድል ታሪክ ስናከብር እኛም ሌላ ድል ለማስመዝገብ በጋራ በመስራት መሆን አለበት ብለዋል።

ከልዩነት ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በማተኮር፤ ከጥላቻ ወጥተን ፍቅርን በመስበክ፤ ከመጣላት ይልቅ እርቅን በመሻት አገራችንን ከድህነት እናሻግር ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአድዋ ድል በኢትዮጵያዊያን የጋራ ትግል የተገኘ ውጤት መሆኑን በመጥቀስ በአገር ልማት ላይ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ አብሮነታችን ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ የምንችለው ከግጭትና ልዩነት ወጥተን በጋራ ማልማት ስንችል ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ አቶ አማን አብዱራሂም ናቸው።

ከጥንታዊ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ልጅ ኤርሚያስ ተሰማ፤ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና ሌሎችም ልዩነቶች ከፋፍለው አገር ሊያሳጡን የተነሱ ጠላቶችን ከምንም አስቀድመን ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ጠላቶች የሚወረወሩ አፍራሽና አሉታዊ ሃሳቦችን ወደ ጎን በመተው አንድነትታችንን በማስጠበቅ ከችግር ለመውጣት በጋራ መስራት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላኛው በዓሉን ሲያከብር ያገኘነው ወጣት ሚኪያስ አበበ፤ በአድዋ ጀግኖች በጋራ የፈፀሙትን ታሪክ የማይዘነጋው ድል እኛም በድህነት ላይ በጋራ ዘምተን ድል ማስመዝገብ አለብን ብሏል።

በተለይም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መከፋፈልን በመተው በአብሮነት ሰርተን የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም