ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የዓድዋ ድል ሚስጢር የሆነውን አንድነት ተጠቅመን የወቅቱን ፈተናዎች ማለፍ ይጠበቅብናል

አርባምንጭ ፤የካቲት 23/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የዓድዋ ጀግኖች የአሸናፊነት ሚስጢር የሆነውን ጠንካራ አንድነት ተጠቅመን ፈተናዎችን በአሸናፊነት መወጣት ይጠበቅናል ሲሉ የደቡብ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ።

ቢሮው ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 126ኛውን የዓድዋ ድል  በዓል በክልል ደረጃ በአርባ ምንጭ ከተማ አክብሯል፡፡

በዚህ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ፤ የዓድዋ ድል ነፃ የወጣንበት ቀን ብቻ ሳይሆን፤ ለቅኝ ገዢዎች አይበገሬነታችንን ያሳየንበትና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆንንበት ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

የጀግኖች አባቶቻችን የአሸናፊነት ልኬት የሆነው የአድዋ ድል ምስጢር ነፃነታቸውን ለየትኛውም ምድራዊ ኃይል አሳልፎ ላለመስጠት በቆራጥነት መነሳታቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

''አንድነታቸው አንድ ቋንቋ በመናገርና አንድ አካባቢ በመኖር ሳይሆን፤ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በመተው የሀገራቸውን ሉአላዊነት ማስቀደማቸው ነበር'' ሲሉም አመላክተዋል ፡፡

የወቅቱ ፈተና የሆነውን ድህነትን እንዲሁም ከፋፋይ አጀንዳዎችንና ሌሎች ችግሮቻቸንን በማለፍ የበለፀገች ዴሞክራሲያዊትና አንድነቷ የፀና ኢትዮጵያን ለመገንባት መተባበር፣ በህብረት መቆምና ወንድማማችነት እንዲጠናከር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

''ከሚከፋፍሉ ጥቃቅን አጀንዳዎች ይልቅ፤ እንደ አድዋ ድል የሁላችን ታሪክና እሴቶች በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪው ህወሓት መመከት ብቻ ሳይሆን፤ ከወጭ አካላት ጋር ሆነው ተላላኪ መንግሥት በማስቀመጥ አፍራሽ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ጠላቶቿን ያሳፈረው ከጀግኖች አባቶቹ በወረሰው ለሀገር ክብር የመዋደቅ ስብዕና መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል የአሁኑ ትውልድ ታሪከን መዘከር ብቻ ሳይሆን፤ የራሱን ዘመን ታሪክ እንዲሰራ የሥነ ልቡና ስንቅም ጭምር እንደሆነው ተናግረዋል፡፡

''በዘመናችን በርካታ ፈተናዎች ከፊታችን ይጠብቁናል'' ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የኢትዮጵያ ዳር ድንበርና የግዛት አንድነት ፀንቶ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍና ሠላሟን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

ልዩነቶችን በቀና መንፈስ በውይይት መፍታትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማጠናከር እንደሚገባም  ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያንን በዓለም መድረክ ያስከበረ ብቻ ሳይሆን፤ የሰው ዘር በሙሉ እኩል መሆኑን በአደባባይ ያስመሰከረ የአባቶቻችን ብርቱ ተጋድሎ ውጤት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ደርዛ ናቸው።

የጀግኖች አባቶች የድል ማጠንጠኛው በአንድነት መቆምና ከጫፍ እስከ ጫፍ ተናቦ መሥራት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

''እኛም እንደአባቶቻችን ታሪክ ለመስራት በጠላቶቻችን ላይ በጋራ መዝመት ይገባናል፤ በመቻቻል፣በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መፍጠር አለብን'' ብለዋል፡፡

ልክ እንደ አባቶቻችን በይቻላል መንፈስ በጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎቻችን ላይ፣ በግዙፍ ልማታዊ ፕሮጀክቶቻችንና ሌሎች ሥራዎቻችን ላይ መረባረብም እንዲሁ፡፡

በተገባዥነት የተገኙት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ በበኩላቸው፤ በወቅቱ የሥልጣኔ ማማ ላይ የነበረችው ቅኝ ገዢዋ አጣልያን ኢትዮጵያን በመውረር የታላቋን ኢጣልያን ግዛት በምሥራቅ አፍሪካ መመስረት አልማ እንደነበር አውስተዋል፡፡

የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደ ሌሎች ሀገራት መሪዎች በመደለያ ሊታለሉላቸው እንደሚችሉ ተስፋ አድርጎ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በየአቅጣጫው ያሉትን በተለይ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቅያሜ ውስጥ የገቡ መኳንንትና መሳፍንት  ማስነሳት ቀላል ነው ብለው ገምተው እንደነበር ከታሪክ መዛግብት ጠቅሰው ፕሮፌሰር ሹመት አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢጣልያን መንግሥት ሸፍጥና ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት የመቀራመት ዓላማ ግልፅ እየሆነ ሲመጣ ብሎም የጦርነቱ አይቀሬነት ዕውን ሲሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የሀገራቸውን ጉዳይ በማስቀደም የክተት ዓዋጁን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአንድ ልብ ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት መዋደቃቸውን አመልክተው፣ ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ ኃይል የማሰባሰብና የማስተባበር ብስለትና ጥበብ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

''በኢትዮጵያ አሁንም ተስፋ አለኝ'' ያሉት ፕሮፌሰር ሹመት፤ ''ልክ እንደ አባቶች ወቅታዊ ፈተናዎችን ለማለፍ በፅናትና በቆራጥነት መስራት ያስፈልጋል'' ብለዋል ፡፡

“ ዓድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት ፤ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ጮራ ” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ ድሉን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ፣ ተውኔቶችና ሙዚቃ ቀርበዋል፡፡

የክልሉ ፣ የዞኑና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንዲሁም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አባትና እናት አርበኞች፣የጋሞ የባህል አባቶችና የሃይማኖት መሪዎች በበዓሉ ላይ ተካፍለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም