የአባቶችን የጀግንነት ወኔ በመላበስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አይደፈሬነት ማስቀጠል ይገባል-ሜጀር ጀነራል አህመድ ሀምዛ - ኢዜአ አማርኛ
የአባቶችን የጀግንነት ወኔ በመላበስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አይደፈሬነት ማስቀጠል ይገባል-ሜጀር ጀነራል አህመድ ሀምዛ
ደሴ የካቲት 23/2014 (ኢዜአ) ''ሁሉም ዜጋ የአባቶቹን የጀግንነት ወኔ በመላበስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አይደፈሬነት ማስቀጠል ይኖርበታል'' ሲሉ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል አህመድ ሀምዛ አስታወቁ።
የአድዋ ድል 126ኛ ዓመት መታሰቢያ በአል በታሪካዊቷ ወረኢሉ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ተከብሯል ።
የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል አህመድ ሀምዛ የአድዋ ድል ሁላችንም ቀና እንድንል ያደረገ፣ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ማህተምና ውጤት ነው” ሲሉ በበአሉ አከባበር በስነ ስርአት ላይ ተናግረዋል።
ድሉ ለመላው አፍሪካ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት፣ የአሸናፊነት መንፈስና የይቻላልን ራዕይ በተግባር ያሳየ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።
በአጼ ምኒሊክ መሪነትና አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ ሆኖ የወራሪውን የኢጣሊያ ጦር ድል አድርጎ ታሪክ ማስመዝገቡን ጠቁመው “እኛም የዘመናችን የጋራ ጠላት የሆኑትን ድህነትንና አሸባሪ ቡድኖችን በጋራ ድል ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል።
ከወራሪው የኢጣሊያ ጦር ጋር የተደረገው ጦርነቶች ለነጻነት፣ ለሉዓላዊነትና ለፍትህ ሲባል የተደረገ መሆኑን ጠቁመው ከአንዳንድ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የተካሄደው የህልውና ዘመቻም ተመሳሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
“ሁሉም ዜጋ የአባቶቹን የጀግንነት ወኔ ተላብሶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይኖርበታል” ያሉት ሜጀር ጀነራል አሕመድ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የሀገርንና ህዝብን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ በሚችል መልኩ እየተደራጀ መሆኑን አስታውቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ ዳኜ በበኩላቸው “ወጣቱ ከአድዋ ድል ተምሮ በአንድነት ኢትዮጵያን መጠበቅና ማልማት ይጠበቅበታል” ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ሉአላዊነታችንን ለማስከበር ያስመዘግናቸውን ድሎች ጠብቆ ከማስቀጠልና ከማልማት ጎን ለጎን በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ከሁላችንም የሚጠበቅ የወቅቱ አጀንዳ ነው “ ሲሉም አክለዋል ።
በአድዋ ጦርነት የክተት ጥሪ የተጠራበት ወረኢሉ፣ የውጫሌ ውል የተፈረመበትን ይስማ ንጉሥን ጨምሮ በዞኑ ለድሉ መነሻ የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ምክትል አስተዳዳሪው ቦታዎቹን በማልማት ትውልዱ ታሪኩን እንዲረዳ ከማድረግ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
''በዓሉ ሲከበር ታሪካዊ ቦታዎችን በመዘከር፣ የድሉን መገኛ ሚስጥር በማውሳት፣ የአባቶቻችንን ገድልና አንድነት በማስታወስ ሊሆን ይገባል'' ያሉት ደግሞ የወረኢሉ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እሸቱ ታረቀኝ ናቸው።
አድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ የተጠራባትን ወረኢሉን ለማስተዋወቅና ለማልማት ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአድዋን ትክክለኛ ታሪክ ተረድታ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን የገለፀችው ደግሞ የወረኢሉ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሀና በላይ ናት።
“በዓሉ በታሪካዊ ቦታዎች መከበሩ የአባቶቻችን ታሪክ እንድንረዳና አንድነታችንንና ሰላማችንን በጋራ እንድንጠብቅ ያግዘናል ብላለች” ።
የበአሉ በፈረስ ጉግስና በተለያዩ ስነ ስርአቶች ተከብሯል።