የሞጆ ከተማ አስተዳደር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ

ሐረር ፤ የካቲት 23/2014(ኢዜአ)የሞጆ ከተማ አስተዳደር በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዛሬ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የሞጆ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ፀጋዬ ተክለሃና ለምሥራቅ ሐረርጌ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ አስረክበዋል።

ዋና አስተዳዳሪዋ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በዞኑ ከዝናብ እጥረት ጋር በተያይዘ አምስት አርብቶ አደር ወረዳዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል፤በዚህም በወረዳዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎችና እንስሳት ለችግር ተጋልጠዋል።

የከተማው አስተዳደር በችግር ውስጥ ለወደቁት ወገኖች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድርቁ በተለይ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በመንግሥት፣የዞኑ ሕዝብና ለጋሾች ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ አደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኑሬ መሐመድ ናቸው።

ሆኖም ለተጎጂዎቹ የሚደርሰው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም  የምግብ ፣ የእንሰሳት መኖና የውሃ አቅርቦት  ድጋፉን  እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

 የሞጆ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በበኩላቸው፤ ድጋፉ በዞኑ በተከሰተው  ድርቅ ለተጎዱት ዜጎች   900 ኩንታል እህል ድጋፍ ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

ድርቁ በዞኑ ከህዝቡ በተጨማሪ እንስሳቱም ላይ ጉዳት ማስከተሉን መገንዘባቸውን ገልጸው፤ በቀጣዩ ሳምንት 1ሺ 600 እስር የእንስሳት  መኖ ለማምጣት ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

የዞኑ አደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት የምግብና የእንሰሳት መኖ ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም