የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ሰቲት ሑሞራ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ሰቲት ሑሞራ ገቡ
ሁመራ ነሀሴ 27/2010 በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ዛሬ ጥዋት ሰቲት ሑሞራ ገቡ፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትና ሰላም መጠናከሩን ተከትሎ የለውጠ አካል ለመሆን ኤርትራ የነበሩት እነዚህ አርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ትጥቃቸውን በመፍታት ነው ወደ ሀገር የተመለሱት፡፡ የትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የፀጥታ አስተባባሪና ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተኪኡ ምትኩ አባላቱን በመቀበል የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የለውጡ አካል በመሆን በሀገራቸው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መምጣታቸው አስደሳች መሆኑንም አቶ ተኪኡ ተናግረዋል ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት መካከል ወታደር ዮናስ አለኸኝ "ሁለቱ መንግስታት ያደረጉት የሰላም ስምምነትና አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በመደገፍ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ገብተናል " ሲል በስፍራው ለሚገኘው ኢዜአ ሪፖርተር በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡ " እኛ የለውጡ አካል ለመሆን ወደ ሀገራችን ገብተናል፤ ለውጡ ዳር ለማድረስም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋልን" ያለው ደግሞ ሌላው አባል ወታደር ጌቱ ዘላለም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ውጭ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ተመልሰው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ባቀረበወ ጥሪ መሰረት ዛሬ በሰቲት ሑሞራ በኩል የገቡት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ከ270 በላይ እንደሆኑ ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግባል፡፡