ቀጥታ፡

በህገ ወጥ የቤንዚን ንግድ ስራቸው መስተጓጎሉን የጭሮ ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ገለጹ

ጭሮ፤የካቲት23/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በጭሮ ከተማ የሚገኙ ባጃጅ አሽከርካሪዎች ህገ-ወጥ ቤንዚን ነጋዴዎች በከተማዋ በመበራከታቸው ምክንያት የዕለት ተዕለት ስራቸው መስተጓጎሉን ገለጹ፡፡  

በጭሮ ከተማ የሚገኙ ባጃጅ አሽከርካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በነዳጅ ማደያ በ31 ብር ሂሳብ የሚገዙትን አንድ ሊትር ቤንዚን ከህገ-ወጥ ቸርቻሪዎች በ70 ብር ለመግዛት ተገደዋል።

ከባጃጅ አሽከርካሪዎቹ መካከል አቶ መኮንን ሻወል እንዳሉት በከተማዋ አምስት የነዳጅ ማደያዎች ቢኖሩም ምሽትን ተገን አድርገው በጀሪካን ለህገ ወጥ ነጋዴዎች በ35 ብር ይሸጣሉ።

በዚህ ሁኔታ ሁለት ሶስት ቀን ይሸጡና አልቋል ስለሚሉ አንድ ሊትር ቤንዚን በ70 ብር ከህገ ወጥ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ለመግዛት እንደተገደዱ ተናግረዋል።

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ አንድ ሊትር ቤንዚን በ70 ብር ገዝተው ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት አዋጭ ባለመሆኑ  የዕለት ተዕለት ስራቸው እየተስተጓጎለ ነው።

"መንግሥት የስራ ፈቃዱን ሲሰጠን በሀገራችን ላይ በፍትሃዊ መንገድ ስሩ ብሎ ቢሆንም ህገ ወጦች በህልውናችን ላይ ቁማር እየተጫወቱ መሆኑ ሊታወቅልን ይገባል" ብለዋል፡፡

ወጣት አሳምነው በበኩሉ ከነዳጅ ማደያ ቤንዚን አውጥተው መንደር ውስጥ በችርቻሮ ከሚሸጡ ህገ ወጥ ቸርቻሪ ነጋዴዎች አንድ ሊትር ቤንዚን በ70 ብር እየገዛ ለኪሳራ መዳረጉን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ እንዳለው ባጃጅ ለከተማው ማህበረሰብ ብቸኛ መጓጓዣ ሲሆን ቤንዚን ማደያዎች ነዳጅ በመጣ ገና በሁለተኛው ቀን አልቋል ስለሚሉ መንቀሳቀስ አልቻልንም ነው ያለው፡፡

የግል ጥቅማቸውን ከህዝብ አገልግሎት ያስበለጡ በመሆናቸውም ምሽትን ተገን በማድረግ በጀሪካን መንግስት ያወጣውን 31 ብር ታሪፍ ወደ 35 ብር ከፍ አድርገው ለህገ ወጥ ነጋዴዎች መሸጣቸው አግባብ አይደለም ይላል፡፡

ወጣት አሳምነው አክሎም ችግሩ በዚሁ ከቀጠለና መስራት ካልተቻለ ቀምሶ የሚያድረውን ስለማግኘቱ ስጋት እንዳደረበት ተናግሯል፡፡

በጭሮ ከተማ የቶታል ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ አብደላ መሀመድ እንደሚሉት የቤንዚን እጥረቱ የተከሰተው የውሃ ሞተር ለሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ቅድሚያ በመስጠቱ ነው፡፡

አንድ አርሶ አደር ስድስትና እና ሰባት የባለ 25 ሊትር ጀሪካን ቤንዚን ሲገዛ አንድ ባጃጅ ደግሞ ስምንት ሊትር ቀድቶ ይሄዳል፡፡

ስራ አስኪያጁ እንዳሉት በዚህም ምክንያት ፍትሃዊነት ላይ የባጃጅ አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ያሰማሉ፡፡

ነዳጅ ከጅቡቲ ተጓጉዞ ጭሮ እስከሚደርስ ድረስ ከሶስት እና አራት ቀናት በላይ ስለሚወስድ በዚህ መካከል የነዳጅ እጥረት ይከሰታል ብለዋል፡፡

ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመከላከል የከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት ተወካዮች ባሉት ለአርሶ አደሮች የቀበሌ ማረጋገጫ ደብዳቤያቸው እየታየ እንደሚሸጥላቸውም ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ከቀበሌ ሊቀመንበር ጋር በመመሳጠር የቀበሌ ማረጋገጫ ወረቀት እያወጡ በህገወጥ መንገድ ግዢ ይፈፅማሉ የሚል ስሞታ መኖሩንም  ጨምረው ገልፀዋል።

አርሶ አደሩን ተመሳስለው ገብተው 31 ብር ገዝተው በ35 ብር እፊታቸው የሚሸጡ ህገ-ወጦች ስማቸውን እያጠፉ መሆኑን ገልጸው፤ በየመንደሩ አንድ ሊትር በ60 እና 70 ብር በመሸጥ ህገ-ወጥነትን ያስፋፋሉም ብለዋል፡፡

ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ለመከላከል እስካሁን ያደረጉት ምንም ጥረት እንደሌለ ጠቅሰው በቀጣይ ግን ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የመከላከል ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የኦልዌይ የነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ውሂባ በበኩላቸው አርሶ አደሩ የመስኖ እርሻው እንዳይስተጓጎል ቅድሚያ እንዲሰጠው ከንግድ ጽህፈት ቤት አቅጣጫ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ አክለውም ለአርሶ አደሮች የቤንዚን ሽያጩ የሚከናወነው የንግድ ጽህፈት ቤት ተወካዮች ባሉበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

“ለአርሶ አደሩም ሆነ ለማንኛውም አሽከርካሪዎች መንግሥት ባወጣው ታሪፍ መሰረት አንድ ሊትር ቤንዚን በ31 ብር ነው የምንሸጠው ብለዋል፡፡”

ቤንዚን በምሽት ሸጠው እንደማያውቁና የንድግ ጽህፈት ቤት ተወካዮች ጠዋት ሲገቡም ምሽት ሲወጡም የቤንዚኑን መጠን የሚለኩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የነዳጅ ንግድ ፈቃድ የሌላቸው ህገ-ወጥ ነጋዴዎች አርሶ አደሩን ተገን አድርገው ለመግዛት የሚያደርጉትንም ሙከራ ከአካባቢው ፖሊሶች ጋር በመሆን እየተከላከሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተማውን ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ አህመድ በሰጡት ምላሽ በከተማዋ በየመንደሩ ህገ-ወጥ ቤንዚን ነጋዴዎች እንዳሉ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ክትትል በማድረግ እንደተረጋገጠ ገልፀዋል።

ቤንዚን በህገ ወጥ መንገድ ከማደያ የሚወጣው በጄኔሬተር ለሚጠቀሙ አርሶ አደሮች በጀሪካ እንዲሸጥ የተሰጠውን ፈቃድ ተገን በማድረግ መሆኑንም እንደደረሱበት ተናግረዋል፡፡

ይህ ችግር የተፈጠረው በምሽት ላይ እስከ አሁን በነዳጅ ማደያዎች ላይ ክትትል አለማድረጋቸው የፈጠረው ክፍተት መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

የጥበቃ ኃይል በመጨመር ከገበያ ማረጋጋትና ቁጥጥር ኮሚቴዎች ጋር ምሽት ላይ የነዳጅ ማደያዎች ከፍተኛ ክትትል ለማድረግ መወሰኑንም ገልጸዋል።

በተደጋጋሚ ቤንዚን በመጣ በሁለተኛው ቀን አልቋል መባሉንና አንዳንዶች ግን በጀሪካን ቤንዚን ገዝተው ሲሄዱ ይታያሉ የሚባለውንም መስማታቸውንና ክትትል እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ነዳጅ በጀሪካን ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር ኬላዎችና ፖሊሶች ክትትል እያደረጉ ከ12 ሰዓት በኋላ ማደያዎች በጀሪካን ቤንዚን እንዳይሸጡ ጥበቃና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችንም ለማወያየትና ለባጃጅ አሽከርካሪዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የማይሸጡ ከሆነ   ተጠያቂ እንደሚሆኑ ለማስገንዘብ ታቅዶ  ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ በተደረገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ባለፈው ሳምንት አራት ህገ-ወጥ ቤንዚን ነጋዴዎች ቁጥጥር ስር ውለው  ለፍርድ ቀርበው በህግ እንዲጠየቁ ጉዳያቸው በምርመራ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም