የብልጽግና ጉዞውን ለማፋጠን ሁሉም የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ጉዞውን ለማፋጠን ሁሉም የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ፤ የካቲት 23/2014(ኢዜአ) ጠላት የሚጠቀሙባቸውን የጸረ-አንድነት እንቅስቃሴ በማምከን የብልጽግና ጉዞውን ለማፋጠን ሁሉም የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አመለከቱ።
"ዓድዋ ለኢትዮጵያውን ህብረት፤ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ" መሪ ሃሳብ 126ኛው የዓድዋ የድል በዓል በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።
በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄራዊ ክብር ማህተም ፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ዓርማ ነው ብለዋል።
ጀግኖች አባቶች በኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ የድል አድራጊነት ብስራት የተጎናጸፉት የነበራቸው አንድነታቸውና የወንድማማችነት ሚስጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑም ትውልድ የጀግኖች አባቶችን የአንድነትና የወንድማማችነት እሴት በማጎልበት ድህነትን ጨምሮ ሌሎች ፈተናዎችን ለመሻገር በጋራ መረባረብ እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይም የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ ጠላት የሚጠቀሙባቸውን የጸረ-አንድነት እንቅስቃሴ ለማምከንና የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ሁሉም የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የዘንድሮው የዓድዋ በዓል እንደ ሀገር ያጋጠሙ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት በመሻገር የልማት ስኬቶች በተመዘገቡበት ማግስት የሚከበር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ገናና ታሪኮች መካከል የዓድዋ የድል ታሪክ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፈሰር ኡቦንግ ኡቻላ ናቸው።
ይህን አኩሪ ገድል አስጠብቆ ለትውልዱ ለማስተላለፍ በዓሉን በየዓመቱ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዓሉ ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ተከብሯል።