አብሮነትን በማጠናከር ድል ማድረግ እንደሚቻል ከአድዋ ድል መማር ይገባል -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነትን በማጠናከር ድል ማድረግ እንደሚቻል ከአድዋ ድል መማር ይገባል -ምሁራን
ሆሳዕና፤የካቲት 23/2014 (ኢዜአ) አብሮነትን በማጠናከር ድል ማድረግ እንደሚቻል ከአድዋ ድል መማር ይገባል ሲሉ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አመለከቱ።
ቀደምት አባቶች አብሮነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር የአድዋን ድል ማስመዝገብ መቻላቸውን ምሁራኑ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድም አንድነቱንና አብሮነቱን በማጠናከር ድህነትን በማስወገድ ለተተኪው ትውልድ የበለፀገች ሀገር ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል ።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ስነሰብ ትምህርት ኮሌጅ ኃላፊና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሀዱ ቀደምት አባቶች ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማስቀደማቸው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ድል መንሳታቸውን ተናግረዋል ።
"ሀገርን አደጋ ላይ ለመጣል የመጣን ጠላት በአንድነት በመመከት በሀገር ሉዓላዊነት እንደማይደራደሩ በአድዋ አሳይተዋል" ሱሉ አክለዋል።
"በወቅቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በፖለቲካ አቋም ልዩነቶችና ያለመግባባቶች ቢኖሩም ለሀገር በአንድነት በመቆም ወራሪውን ለማሳፈርና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ወሰን ሳይገድባቸው በመትመም ነፃነቷ የተጠበቀ ሀገር አስተላልፈውልናል" ብለዋል።
"የአድዋ ድል ትውልዱ የሀገርን ክብር አስጠብቆ ለማቆየት አብሮነትንና አንድነትን ማጠናከር ብቸኛ መንገድ መሆኑን ያሳየ" መሆኑን አመልክተዋል።
''ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው የብሔር ፖለቲካ አብሮነትን ተፈታትኗል'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ የተዘሩብን የልዩነት አጀንዳዎች ውጤት አልባ መሆናቸውን በሚገባ ስላየን ትውልዱ ከመሸከም ይልቅ አሽቀንጥሮ ሊጥላቸው ይገባል " ብለዋል።
"የዛሬ አብሮነታችን ለነገዋ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ያደገችና ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የመከባበርና የመቻቻል ባህላችንን ማጎልበትና በየዕለት ህይወታችን መተግበር ይገባናል "ሲሉ አክለዋል።
ለሀገር ህልውና መቆየት የቀደምት አባቶች ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በመትመም በአድዋ በከፈሉት መስዋእትነት የሀገርን ህልውናን በማቆየት የማይረሳ ታሪክ ትተዋል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ጉዳዮች ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሙላለም ኃይለ ማርያም ናቸው።
ቀደምት አባቶቻችን በሀገሪቱ ላይ የተቃጣን የጠላት ወረራ መመከት የቻሉት ዘመናዊ መሳሪያ ስለታጠቁ ሳይሆን አንድነታቸውን በማጠናከርና በሀገር ፍቅር መሆኑን ትውልዱ ሊያውቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
''የዜጎች አብሮነት መጠናከር የሀገርን ህልውና አስጠብቆ ለማስቀጠል ከዘመናዊ መሳሪያም በላይ አቅም እንዳለው ጭምር ቀደምት አባቶቻችን በተግባር አስተምረውናል'' ብለዋል።
አሁን ላይ ልዩነቶችን በማስፋት የሀገርን ህልውና ለመፈታተን የተለያዩ ሴራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ''ከቀደምት አባቶቻችን በመማር አንድነታችንን ማጠናከር ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው'' ሲሉ አመልክተዋል።
የአደዋን ድል በልማት በመድገም የበለፀገች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገር ሉዓላዊነት እና ነጻነት እንደማይደራደሩ ያስመሰከሩበት አንጸባራቂው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዛሬው እለት ለ126ኛ ጊዜ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከበረ ነው።