ቀጥታ፡

የሀዋሳ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅና ወንጀልን ለመከላከል የጸጥታ ኃይሉ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ

ሀዋሳ ነሀሴ 27/2010 የሀዋሳ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅና የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ ኃይሉ በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፈው ረዕቡ እና ሐሙስ ሁለት ሰዎች በስለት ተወግተው ህይወታቸው አልፏል፡፡ "ይህንን ተከትሎ ህብረተሰቡ ስጋት ውስጥ ገብቶ ነበር" ያሉት  አዛዡ ክትትሉን በማጠናከር ከዚያ ወዲህ ያጋጠመ ወንጀልና የጸጥታ ችግር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ የግድያ ወንጀሉ የተፈጸመው በገብርኤል ቀብር አካባቢ እና ሂጤታ ቀበሌ መንደር ውስጥ ሲሆን በድርጊቱ የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ተይዘው  ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ሳምንታት 13 የሞባይልና ቦርሳ ንጥቂያ ወንጀሎች ተፈጽመው አብዛኛዎቹ በህዝብና በፖሊስ ትብብር ወዲያው መያዛቸውን አዛዡ አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹን የመከታተል ስራ ፖሊስ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው " ከተያዙት መካከል አምስቱ ወዲያው ውሳኔ አግኝተዋል ፤ ቀሪ አምስቱ በሂደት ላይ ናቸው" ብለዋል፡፡ አዛዡ እንዳመለከቱት የከተማና ክልል ፖሊስ ፣ ልዩ ኃይል ፣ የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት በመቀናጀት የስጋት ቀጠና በሆኑ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የከተማውን ሰላም ለማስጠበቅና የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ "የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ በተጠናከረባቸው መንደሮች ህብረተሰቡ አካባቢውን እየጠበቀ በወንጀል መከላከሉ እገዛ እያደረገ ነው" ያሉት ፖሊስ አዛዡ የሰላሙ ባለቤት ህዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከነሃሴ 20 ጀምሮ በከተማዋ የተቃውሞ ሰልፍ ይኖራል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ  የሚለቀቀሉ መረጃዎች ከእውነት የራቁና የከተማዋን ሰላም በማይፈልጉ የሚነዛ የሀሰት ወሬ በመሆኑ ህዝቡ ይህንን ተገንዝቦ መረበሽ እንደሌለበትም አዛዡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ህጋዊውም ይሁን ህገ ወጥ ሰልፉ ከመንግስት እውቅና ውጭ እንደማይሆን ጠቅሰዋል፡፡ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የሚጥሉ ጉዳዮች እንዳይኖሩ በየክፍለ ከተማው የህዝብ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም ፖሊስ አዛዡ ጠቁመዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ወንጀልን ለመከላከል ከጸጥታ ኃይሉን ጋር በመተባበር እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም