ቀጥታ፡

አያቶቻችን የአድዋን ድል በጋራ እንዳሳኩ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ድህነትን በጋራ ተዋግቶ ድል ማድረግ አለበት

የካቲት 23/2014 (ኢዜአ) የቀደሙት አያቶቻችን የአድዋን ድል በጋራ እንዳሳኩ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም በጋራ ልማት ድህነትን ማሸነፍ እንዳለበት የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለጹ።

126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ ዛሬ ላይ አድዋን የምናከብረው ከ126 ዓመት በፊት የነበሩ አያቶቻችን ወራሪዎችን በጋራ አሸንፈው ባስመዘገቡት ድል ነው ብለዋል።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድም ድህነትን በጋራ ተዋግቶ በማሸነፍ ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች አገር የማስረከብ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በዘውግና ማንነት፣ በሃይማኖትም ሆነ ብሄር ሳንለያይ ለአገር ልማት በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የጀመረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ታሪክ በመስራት ደማቅ አሻራችንን ማኖር አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነት አብሮነትን ለማደብዘዝ፤ አሁንም ቅኝ ሊገዙንና ታሪካችንን ሊነጥቁን የሚሹ ከሃዲዎች አሉ በማለት የጠቀሱት ዶክተር አረጋዊ የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በዚህ ትውልድም ተጠብቆ መዝለቅ አለበት በማለት ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገራችን ታላቅ ተስፋ ለአህጉራችንም የብርሃን ጮራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በጋራ ጥረታችን በማሳካት አገራችንን ማልማት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ፤ በበኩላቸው የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውን ህብረት ለአፍሪካውያን የነጻነት ጮራ የፈነጠቀ ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን አባቶች ወደር በሌለው ጀግንነት ተዋግቶ በአንድነት በመቆም አገርን ከወራሪዎች ታድጓል ነጻነትንም አውርሰዋል ብለዋል።

የራሳቸውን ሃብት ለማካበት ወራሪዎች ሃብት ለመቀራመት የነበራቸውን ህልም ጀግኖች አያቶቻችን አሳፍረው በመመለስ ክብርና ነፃነት አጎናፅፈውናል ሲሉ ተናግረዋል።

"የጀግኖች የድልና አሸናፊነት ትልቅ ሚስጥር የአገር ፍቅር ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የአሁኑ ትውልድም ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ መቆም አለበት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያን ሁላችንም በማልማት፣ ሰላምና አብሮነትን በማጠናከር ብልጽግናችንን በጋራ እናረጋግጥ ብለዋል።

የዘንድሮው 126ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም