ቀጥታ፡

የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ወጣቶች በታላቅ ኃላፊነት ሊሰሩ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ  ነሀሴ 27/2010 በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዳይስተጓጎል ወጣቶች በታላቅ ኃላፊነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስገነዘበ። የደቡብ ወጣቶች ማህበር አዲስ አበባ ቅርጫፍ የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት በዓል ዛሬ አክብሯል። ''ክልላዊና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ለወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንተጋለን'' በሚል መሪ ሀሳብ ነው በዓሉ የተከበረው። የቢሮው ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀንበር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት አገሪቷን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተለያዩ የለውጥ አቅጣጫዎች ተቀይሰው እየተተገበሩ ነው። ''ይህ የለውጥ እንቅስቃሴ ተስፋ የሚታይበት ነው'' ያሉት ኃላፊው ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወጣቶች ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ  አቅርበዋል። በተለይም ለአገሪቱ አንድነት ፈተና የሚሆኑ ጉዳዮችን በመታገል ረገድ ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው ኃላፊው ያስገነዘቡት። "ለውጥ የሚጀምረው ከግለሰብ ነው፤ በመሆኑም ወጣቶች በቅድሚያ እራሳቸውን በመለወጥ ለአገር የለውጥ ሂደት ለመሥራት መዘጋጀት  አለባቸው፤" ሲሉም አቶ ጀማሉ መክረዋል። የደቡብ ወጣቶች ማህበር አዲስ አበባ ቅርጫፍ ፕሬዝዳንት ወጣት አብረሃም ፈቃዱ በበኩሉ ማህበሩ ወጣቶች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ነጻ የክርክርና ውይይት መድረኮችን በተለያዩ ጊዜያት ማዘጋጀቱን ይገልጻል። በተለይም በክረምት በጎ-ፈቃድ አገልግሎት ላይ የማህበሩ አባላትን በተለያዩ መስኮች በማሳተፍ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም 350 የሚሆኑ ወጣቶች በትራፊክ ፖሊስ ዘርፍ ተሰማርተው የበጎ-ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ወጣት አብረሃም አመልክቷል። ከዚህም ሌላ ከ200 የሚልቁ ወጣቶች ደም መለገሳቸውን አብራርቷል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመደገፍ በተደረጉ እንቅስቃሴዎችም ማህበሩ ከ350 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት በስጦታ ማበርከቱን ተናግሯል። እንደ ወጣት አብርሃም ገለጻ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ከ 1 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል፤ በመስኩም የተሻለ ልምድ ያላቸው ወጣቶች ለመሰሎቻቸው ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ዕድል ተፈጥሯል። ''በቀጣይም በአገር ፍቅር፣ በመደመርና በይቅርታ ስሜት ከቂም በቀልና ጥላቻ በመራቅ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ቃላችንን ማደስ ይኖርብናል'' ሲልም ተደምጧል። በበዓሉ አከባባር ላይ ለደቡብ ወጣቶች ማህበር አዲስ አበባ ቅርጫፍ  ስኬት በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት ማህበሩ 2 ሺህ ወጣት አባላት ያሉት ሲሆን ከ 10 ሺህ በላይ ደጋፊና የክብር አባላት እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል። ማህበሩ በ2000 ዓ.ም በጥቂት የክልሉ ተወላጆችና አባላት መመስረቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም