የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተሰባስበው ታሪክ የሰሩበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተሰባስበው ታሪክ የሰሩበት ነው
የካቲት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሰባሰብ ታሪክ የሰሩበት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ተናገሩ።
የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይ የተለያየ ስነ ስርዓት ተከናውኗል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች እና ሌሎች እንግዶች ታድመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ በወቅቱ እንዳሉት፤ የአድዋ ድል መላ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው የጣሊያን ወራሪ ኃይል አሳፍረው የመለሱበት እለት ነው ብለዋል፡፡
ቀደምት አባቶች በመስዋዕትነት ነጻ አገር አስረክበውናል፤ ክብርም ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የአሁኑ ትውልድም የቀደምት አባቶቹን የአሸናፊነት መንፈስ በመውረስ አገር ሊያፈርስ የተነሳውን የህወሃት የሽብር ቡድንን ድል በመንሳት የአገር አንድነት ማስጠበቁንም ጠቅሰዋል፡፡
126ኛውን የአድዋ ድል ስናከብር ድህነትን በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለመውሰድ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ከፋፋይ የሆኑ አካሄዶችን በመተው አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከር አለብን ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡