የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን ከቅኝ ገዢዎች በመታደግ ነጻነቱን ያስከበረበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን ከቅኝ ገዢዎች በመታደግ ነጻነቱን ያስከበረበት ነው
የካቲት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች በመታደግ ነጻነቱን ያስከበረበት ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌይ ተረክሂን ገለጹ።
የአድዋ ድል በዓል ለኢትዮጵያ የነጻነት ምልክት ነው ብለዋል።
አምባሳደር ሰርጌይ ተረክሂን 126ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአድዋ ድል በዓል ለኢትዮጵያ የነጻነት ምልክት ነው፤ ድሉ የኢትዮጵያ አገረ መንግስት በማጠናከር ኢትዮጵያ የራሷ የአገር ውስጥና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲኖራት ያደረገ ጠንካራ ሃይል እንደሆነም ገልጸዋል።
“የአድዋ ጦርነት ያለ ምንም ማጋነን በባርነት ይኖሩ ለነበሩ የአፍሪካ ሕዝቦች ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ ላደረጉት ትግል መሪ ኮከብ ነበር” ብለዋል አምባሳደር ሰርጌይ።
የአድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት የመጀመር ሂደት ውስጥ ታሪካዊ ስፍራ እንዳለው አመልክተዋል።
“የሩሲያ ተወካዮች በጦር ሜዳ ለተገኘው ድል በግላቸው አስተዋጽኦ አድርገዋል” ያሉት አምባሳደሩ፤ የሩሲያ ሕክምና ባለሙያዎች በጦርነቱ የቆሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወት በማዳን እርዳታ እንዳደረጉ ተናግረዋል።
የአድዋ ጦርነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመራቸውንና የአድዋ ድል በሁለቱ አገራት የግንኙነት ታሪክ ጠንካራ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር ሰርጌይ ተርክሂን በዚህ ታሪካዊ ቀን ለኢትዮጵያ ወንድም ሕዝብ ሰላም፣ ብልጽግናና ስኬትን እንደሚመኙ መግለጻቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼