ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ በክብር የመዝለቅ አመክንዮ የዜጎቿ አንድነት ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ ነው

የካቲት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ በክብር የመዝለቅ አመክንዮ የዜጎቿ አንድነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን 126ኛ የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-ለመላው ኢትዮጵያውያን! እንኳን ለ126ኛ የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በረጅሙ የታሪክ ጉዞ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተው ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን መዳፈራቸው በግልፅ ይታወቃል።

በዘመን ሰንሰለት ሃገራችን በውስጥ እና በውጭ ጠላቶች የተቃጡባትን የጦርነት ጥቃት ተከትሎ፤ ድፍረትን በሚጠየፉ ጀግና ልጆቿ ፈታኝ አውዶች በድል እየተሻገረች እነሆ በክብር ዘልቃለች።

ሃገራችን ኢትዮጵያ በክብር የመዝለቋ አመክንዮ በዜጎቿ አንድነት እና ህብረት ጥንካሬ ላይ እንደተመሰረተ አያሌ ቱባ የታሪክ አብነቶችን ለማሳያነት በኩራት መምዘዝ ይቻላል።

በትውልድ ቅብብሎሽ ከተመዘገቡት ቱባ የታሪክ አብነቶች መካከል የአድዋ ድል በዓል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ታላቅ ማሳያ ሲሆን፤ በቀደመው፣ በአሁኑ እና በሚቀጥለው ዘመን በከፍታ የሚዘከር የድል ወረታችን ነው።

የአድዋ ድል በዓል ትናንትን በፅናት፤ ዛሬን በወኔ እንዲሁም ነገን በቁርጠኝነት የሃገራችን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ሳይሸራረፍ በክብር እንድትዘልቅ በትውልድ ልቦና የድል አድራጊነት መንፈስ የሚያጋባ የወል እሴታችን ነው።

የአድዋ ድል በዓል የሃገር ሉዓላዊነት እና ነፃነት የማስከበር ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ፤ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት መከበር ለፈጠረው ንቅናቄ የድል አድራጊነት ውሃልክ ያሰመረ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው።

በእኛ ዘመን እና ትውልድ ሃገራችን ሉዓላዊነቷን ከሚዳፈሩ እና ነፃነቷን ከሚፈታተኑ ሃይሎች የተቃጡ መልከ ብዙ ጥቃቶችን በጋራ በመመከት አንድነቷን ጠብቃ ጉዞዋን ወደፊት ቀጥላለች።

በዘመናችን ሃገራችን የገጠሟትን ከባድ እና ውስብስብ ጥቃቶችን መመከት የተቻለበት ምስጢር ከቀደሙ አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ለአሸናፊነት ያበቃቸውን ወኔ በመውረስ እንዲሁም አንድነታችንን አጥብቀን እና ጠብቀን መጓዝ በመቻላችን ነው።

አሁንም ቢሆን በሃገር ሉዓላዊነት እና ነፃነት ዙሪያ የሚቃጡብንን ጥቃቶች በፅኑ አንድነት እየመከትን፤ በዕድገት ጉዞ ከፊትለፊት የሚጠብቁንን ውስብስብ ፈተናዎች እንድንሻገር ህብረታዊ የድል ልምምዳችንን በተግባር እንድናረጋግጥ አደራ ለማለት እወዳለሁ።መልካም የአድዋ ድል በዓል!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም