ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ በ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የስልጠና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የካቲት 22/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የስልጠና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ባለስልጣኑ ማዕከሉን ያስገነባው ከጣልያን የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ሲሆን፤ ማዕከሉ የቡና ምርት ላይ እሴት መጨመር የሚያስችል ስልጠና ይሰጣል ነው የተባለው፡፡

ማዕከሉን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እና የጣልያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪና ሴሬኒ በይፋ ስራ አስጀምረዋል፡፡

ማዕከሉ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኝውን ጥቅም በማሳደግ ረገድ የጎላ ሚና አለው ተብሏል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ እሴት የተጨመረበት ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከዘርፉ የሚገኘውን አገራዊ ጥቅም ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ የስልጠና ማዕከሉ ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራረት እንዲኖር

ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ነው ያነሱት፡፡

ማእከሉ ቡና ለሚቀምሱ፣ እሴት ለሚጨምሩና በቡና ማፍያ ማሽን ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸው፤ ወጪውም ሙሉ በሙሉ በጣልያኑ የልማት ድርጅት እንደተሸፈነ ጠቁመዋል።

ማዕከሉ በቀጣይ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸውን አዎንታዊ ሚና የሚያበረክቱ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የጣልያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪና ሴሬኒ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ጣልያን መልካም ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ማዕከሉ በተለይ ወጣቶችን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

በተያያዘ ዜና ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማሪና ሴሬኒ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ፈጠራ ማዕከልን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም