ቀጥታ፡

የአድዋ ድልን የአንድነትና የትብብር መንፈስ ለዲፕሎማሲው መስክ ስኬት እንደ ግብዓት መጠቀም ይገባል

የካቲት 22/2014/ኢዜአ/   የአድዋ ድልንን የአንድነትና የትብብር መንፈስ በመጠቀም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በዲፕሎማሲው መስክ አመርቂ ውጤት ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናኔ መስፋፋትና ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ያበረከተውን አስተዋጽዖ በተመለከተ ምክክር ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እንደገለጹት፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ኅዝቦች በጋራ በመሆን ያስገኙት ድል ነው።

ድሉ ኢትዮጵያዊያን መብታቸውንና ክብራቸውን እንዲያስጠብቁ ከማድረጉ በዘለለ ድንበር ተሻግሮም ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

ድሉ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሲቆሙ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ገልጸው በአንጻሩ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአፍሪካ የነበረውን አሉታዊ አመለካከት የቀየረ ክስተት መሆኑን ጠቁመዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የአድዋ ድል በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ለነጻነታቸው ቀናዒ እንዲሆኑና ለመብታቸው እንዲዋደቁ የአርአያነት ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ጭምር ኩራት የሆነው የአድዋ ድል የተገኘው ሕዝቦች በኅብረትና አንድነት በመቆማቸው መሆኑን ጠቁመው ይህንን መልካም እሴት አዳብሮ መጠቀም እንደሚገባ   አሳስበዋል።

በተለይም ይህንን የአድዋ ድል የአንድነትና የትብብር መንፈስ በመጠቀም በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በዲፕሎማሲው መስክ አመርቂ ውጤት ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ እድገትና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ወጣቱ ትውልድ ዘመን ተሻጋሪ ድል በመቀዳጀት የአድዋን የድል መንፈስ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካውያን የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች እየገጠማቸው መሆኑን አንስተው እነዚህን ችግሮች ለማለፍ የአድዋ አይነት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም አፍሪካውያኖች እርስ በእርሳቸው በመተባበርና በአንድነት በመቆም በፖለቲካውና በምጣኔ ኃብት የሚገጥማቸውንም ከባድ ተግዳሮቶች አሸንፈው መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ጭምር ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህንን አንጸባራቂ ድል ይበልጥ ገናና ለማድረግ ኢትዮጵያዊያኖች ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ የአድዋ ድል ክብረ በዓል ታስቦ እንዲውል ለማድረግ በአገር ውስጥ ያለው ደማቅ አከባበር ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን 1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በአንድነትና በጥበብ ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ድል በማድረግ ለጥቁሮች ነጻነት የሆነውን አኩሪ ታሪክ ማስመዝገባቸው ይታወሳል።

የዘንድሮው 126ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ኃሳብ በነገው ዕለት በድምቀት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም