አንድነታችንን በማጽናት ኢትዮጵያን የማሻገር ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን በማጽናት ኢትዮጵያን የማሻገር ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል
ድሬዳዋ የካቲት 22/2014(ኢዜአ) ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጽናት ኢትዮጵያን የማሻገር ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዑባህ አደም ተናገሩ።
በዩኒቨርሲቲው ''ዓድዋ! የኢትዮጵያና የጥቁር ህዝቦች የሉዓላዊነት መገለጫ'' በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በሥነ -ሥርዓቱ ላይ የዩነቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዳመለከቱት፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው ጥቁር ህዝቦች የማንነትና የነፃነት ምልክት የሆነ ታላቅ ድል ነው።
አባቶቻችን ለሀገር ነፃነትና ለብሔራዊ ኩራት በህብረ-ብሔራዊ አንድነት ተባብረው የፈፀሙት ታላቅ ገድልና ድል መቼም የሚዘከር የሀገር ሃብትና መመኪያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከምዕተ ዓመት በፊት በከፍተኛ ደረጃ ታጥቆ የመጣውን ጠላት በማሸነፍ የተመዘገበውን ድል ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ በማሻገር ላይ መድገም እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ለዚህም ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመውጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
በተለይ የተማረውና አዲሱ ትውልድ ከዚህ ታላቅ መስዋትነት ከተከፈለበትና የአንድነት ውጤት ከሆነው ድል በመማር ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት መረባረብ እንዳለበት ነው ያመለከቱት፡፡
ኢትዮጵያዊያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጽናት ኢትዮጵያን የማሻገር ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉ ዶክተር ዑባህ ተናግረዋል፡፡
''ድሉ ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነትን በር የከፈተና የኢትጵያን ታላቅነት ያረጋገጠ የትውልድ ኩራትና መመኪያ ነው'' ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ናቸው፡፡
ከዓድዋ ድል፣ ከአባቶቻችን መተባበርና መደማመጥን በመማር ኢትዮጵያን ከበለፀጉ ሀገሮች ተርታ ለማስገባት ኃላፊነችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የዓድዋ ድል ትሩፋቶችን በሚያስገነዝቡና በቀጣይ ሀገራዊ ዕድገት ላይ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በበዓሉ የተሳተፉት ምሁራን፣ የሲቪክ፣ የፍትህና የፀጥታ ተቋማት ተወካዮች የፀና ህብረትና አንድነትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሃይልን ያሸነፈችበትን 126ኛ የድል በዓል ነገ ታከብራለች።