ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

የካቲት 22/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ያላትን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ያለውን አገራዊ አቅም ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ያለመ መድረክ ያካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩም በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን የሚመለከት ገለጻ ተደርጓል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በዚሁ ግዜ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ከአፍሪካ የተሻለ ቴክኖሎጂና ባለሙያ ካላቸው አገራት ተርታ ትመደባለች።

በዘርፉ ሳተላይት ከማምጠቅ ጀምሮ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም አሟጦ ከመጠቀም አኳያ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ ተቋማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር በዘርፉ ያለው አቅም ጥቅም ላይ እንዲውል ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የብዝሃ-ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው፤ይህም የመሬት ምልከታ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኢንስቲትዩቱ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በዘርፉ ለሚደረጉ የምርምር ስራዎች በእጅጉ እንደሚያግዙ መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የጤና፣ ግብርና እና የሚቲዎሮሎጂ ዘርፍ ተመራማሪ አቶ ሳሙኤል ራህመቶ፤ ከዚህ ቀደም ለምርምር ስራዎች የሚሆኑ ትክክለኛ መረጃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ኢንስቲትዩቱ ባቋቋመው የብዝሃ-ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ አማካኝነት ትክክለኛ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም በዘርፉ የተሻሉ የምርምር ስራዎችን ለመስራት ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ የሚታወቅ ቢሆንም በሳተላይት የተመረኮዘ መረጃን በመጠቀም ረገድ ክፍተት መኖሩን የገለጹት ደግሞ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ነጻነት ወርቅነህ ናቸው።

በተለይም በግብርና፣ አካባቢ እንክብካቤ፣ ደን ልማት እንዲሁም በአገራዊ ደህንነት ረገድ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን በቀረበው ገለጻ መገንዘባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ተቀራርበው በመስራት ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም