ቀጥታ፡

ቀደምት አባቶች በአድዋ የተጎናጸፉትን ድል የአሁኑ ትውልድ በኢኮኖሚ ዘርፍ ሊደግመው ይገባል

የካቲት 22/2014/ኢዜአ/ ቀደምት አባቶች በአድዋ የተጎናጸፉትን ድል የአሁኑ ትውልድ ድህነትን በማሸነፍ በኢኮኖሚ ዘርፍ ሊደግመው እንደሚገባ የታሪክ ጸኃፊና ተመራማሪ ምሁራን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ጀግኖች ከዛሬ 126 ዓመታት በፊት በአድዋ ተራሮች ላይ አገራቸውን ለመቀራመት በመጣ የጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ ከፍተኛ ድልን ተቀዳጅተዋል።

ድሉም ለመላ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ፤ ለባዕዳን ወራሪ ኃይል ደግሞ ቅስም የሰበረ አኩሪ ገድል ሆኖ አልፏል።

የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ፤ የአድዋ ድል አውሮፓዊያን አፍሪካን እንደቅርጫ ተቀራምተው ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ብዝበዛ እያደረጉ በነበረበት ወቅት የተገኘ የነፃነት ብርሃን መሆኑን ያነሳሉ።

ሌላኛው የታሪክ ጸኃፊና ጋዜጠኛ ተሾመ ብርኃኑ፤ በውጫሌ ውል አንቀጽ-17 መሰረት የኢትዮጵያን የምታካሂዳቸውን የውጭ ግንኙነቶች በሚመለከት የአማርኛና ጣሊያንኛው ትርጓሜ መቃረን እንደነበር ያስታውሳሉ።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ አፄ ምኒሊክ ከአውሮፓውኑ ጋር ግንኙነት ለማድረግ በሚፈልጉበት ወቅትም "በውጫሌ ውል መሰረት ነው ልንገናኝ የምንችለው" የሚለው ምላሽ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ክስተት እንደነበር ይገልፃሉ።

ሁኔታውን ለመቀየርም አጼ ምኒሊክ በቀጥታ የውጫሌውን የውል ሥምምነት ያፈረሱ መሆናቸውን በአዋጅ በይፋ አስነግረው መሻራቸውን አመላክተዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ልዩነት ባገኙት መሳሪያ ጠላትን ተፋልመዋል፤ ዘመናዊ ትጥቅ ያነገበውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይም አኩሪ ድልን ተጎናጽፈዋል፡፡

ምንም እንኳን የግለሰቦች ቁርሾ፣ አስተዳደር በደል፣ የፍትህ መጓደልና የኢኮኖሚ መዛባት ሊኖር ቢችልም በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃትን በጋራ መመከት እንደሚገባ የአድዋ ድል በግልጽ እንደሚያሳይ  ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድ በመቻቻል፣ በመተባበርና በመፈቃቀድ የቀደምት አባቶችን አልበገር ባይነት መንፈስ ተላብሶ ኢትዮጵያን በተሻለ የኢኮኖሚ ከፍታ ላይ ማስቀመጥ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በውድ የህይወት መስዋትነት በከፈሉት ደማቅ ዋጋ 126ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የዓድዋ ድል በአገር ዓቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም