የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት "ምስጢራዊ ነው" በሚል የሚከለክሉ አስፈፃሚ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት "ምስጢራዊ ነው" በሚል የሚከለክሉ አስፈፃሚ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል
አዲስ አበባ የካቲት 22/2014(ኢዜአ) የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት "ምስጢራዊ ነው" በሚል የሚከለክሉ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።
በአስፈፃሚ አካላት የሚደርስን በደል በሚመለከት ለዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት ለመከላከል "የኬዝ ማኔጅመንት ሲስተም" ለመገንባት በሂደት ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፤ ተቋሙ ከሁለት አዋጆች የሚመነጭ ስልጣን እንደተሰጠው ይናገራሉ።
ሆኖም በአስፈፃሚ አካላት የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን የመመርመርና የመፍትሄ ሀሳብ በማቅረብ ተፈፃሚ እንዲሆን የማድረግ ስልጣን በመንግስት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ተፈፃሚ ማድረግ ሳይችል ለዓመታት ዘልቋል ብለዋል፡፡
በዚህም ተቋሙ የፓርቲ ውግንና እንዳለውና ተገልጋዩ በገለልተኛነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳለው የተቋሙን የአስር ዓመት እንቅስቃሴ በተመለከተ ባደረግነው ጥናት አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከነበረበት የተዓማኒነትና ገለልተኝነት ጥያቄ በመውጣት ትክክለኛ የህዝብ እንባ አባሽ ለማድረግ ነፃ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም በአስፈፃሚ አካላት የደረሱ አስተዳደራዊ በደሎችን በመመርመር ያስቀመጣቸው የመፍትሄ ሃሳቦችን ተፈፃሚ በማድረግ በኩል ስኬቱ 48 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት 52 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
በአስፈፃሚ አካላት አስተዳደራዊ በደል የሚደርስባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አቤቱታቸው መፈታት እንዳለበት እናምናለን የሚሉት ዶክተር እንዳለ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ግጭት ለስራቸው እንቅፋት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
በአማራ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ተንቀሳቅሶ ለመስራትም ሆነ በደል የደረሰባቸው ግለሰቦች ወደ እኛ መጥተው አቤቱታ ማቅረብ አልቻሉም ብለዋል፡፡
በአሰራር ውስንነት ካልተፈቱ ችግሮች በተጨማሪ የሙስና፣ የግለሰብ፣ የኦዲትና መሰል ከተቋሙ ስልጣን ጋር የማይያያዙ ጉዳዮች እንደሚቀርቡላቸውም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ቢታወቅም በአንዳንድ ተቋማት በኩል "ምስጢራዊ ነው" በሚል ሰበብ መረጃ የሚከለክሉ አስፈፃሚ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የመከላከያ፣ ፖሊስና የመረጃ ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም እንደ ቴሌና አየር መንገድ ያሉ ተቋማት ካላቸው ምስጢራዊ መረጃ በስተቀር አብዛኞቹ ተቋማት ከህዝብ የሚደበቅ መረጃ ሊኖራቸው አይችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 እና ከመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ መተግበር ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ለማስፈጸም ሲባል እንቅፋት የሚሆኑ አስፈፃሚ አካላትን በአቃቤ ህግ በኩል ክስ ይመሰርታል፣ በመገናኛ ብዙሃን ይጋለጣል፤ በልዩ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባልም ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ለነበረው ምክር ቤት ቀርቦ የነበረውን 42 ልዩ ሪፖርት እንደገና በማደራጀት ለማቅረብ በሂደት ላይ እንገኛለን ሲሉም ዶክተር እንዳለ ገልጸዋል።
አስፈፃሚ አካላት በዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን አስተዳደራዊ በደል ለመከላከል በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን እንገኛለንም ብለዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ 680 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ "ኬዝ ማኔጅመንት ሲስተም" የተባለ አሰራር ለመገንባት በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአሰራር ተቋሙ ከዘረጋው 7502 ነፃ የስልክ ጥሪ በተጨማሪ በክልል ከተሞች ብቻ የታጠረውን የተቋሙን ቅርንጫፍ ወደ ዞን ለማውረድ እየተሰራ ይገኛል።