ከአድዋ ድል የወረስነውን የጦር አመራር ጥበብና ጀግንነት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን - ኢዜአ አማርኛ
ከአድዋ ድል የወረስነውን የጦር አመራር ጥበብና ጀግንነት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን
የካቲት 22/2014(ኢዜአ) ከአድዋ ድል የወረስነውን የጦር አመራር ጥበብና ጀግንነት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ አየር ኃይል አባላት ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ አየር ኃይል በራዳር ሙያና በአየር ውጊያ መስክ አገራቸውን ለ34 ዓመታት ያገለገሉት ኮሎኔል ብርሀኑ አሳምነው እና ሻለቃ ከበደ ለማ ዘገዬ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ መሆኑን ይናገራሉ።
አድዋ የኢትዮጵያዊነት ማንነት እና የነጻነት ጉልበት የታየበት፤ እንዲሁም ቀደምት ኢትዮጵያዊያን የጦር አመራረ ጥበብን ያስመሰከሩብት ታሪካዊ ሁነት እንደሆነ ይገልጻሉ።
የአጼ ምኒልክ የአዋጅ ጥሪን ተከትሎ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የዘመቱ ኢትዮጵያዊያን አድዋ ላይ በህብረት ጠላትን ድል መንሳታቸውን አስታውሰው፤ ይህ የጀግንነት እሴት ዛሬም ህያው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ሰራዊት አባል ከአድዋ ድል የአገር ፍቅር እና የጀግንነት ወኔ ወርሰናል ሲሉም ነው የቀድሞ ሰራዊት አባላቱ የሚናገሩት፡፡
ከአድዋ እሴቶች መካከል የአመራር ጥበብና ብልሃት፣ እውቀትና ሐቀኝነትን መውረስ የእያንዳንዱ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይ ወጣቶች የሁሉም ጥቁር ህዝቦች ምልክት ከሆነው የአድዋ ድል ትምህርት ቀስመው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡