ቀጥታ፡

ዓድዋ የመላው የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው-አባት አርበኞችና የታሪክ ምሁራን

ጂንካ፤የካቲት 22/2014(ኢዜአ)፡የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላው ጥቁር ህዝቦች ከባርነት ነፃ መውጣት እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ ታሪካዊ ድል ነው ሲሉ አባት አርበኞችና የታሪክ ምሁራን ተናገሩ ።
በደቡብ ኦሞ ዞን የጂንካ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የታሪክ ፀሐፊ፣መምህር እና አባት አርበኛው አቶ ደሳላኝ ገብረሚካኤል ''የአድዋ ድል የኛ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላው የጥቁር ህዝቦች ከባርነት አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ በር የከፈተ የይቻላል መንፈስን ያሰረፀ ታሪካዊ ድል ነው'' ብለዋል።

የዓድዋ ድል የነጮችን  ገዢነትና የጥቁሮችን ተገዢነት የተገባ ተደርጎ በወቅቱ ይታይ የነበረውን ዓለም አቀፍ እይታ የቀየረ ትርጉሙ ከአንድ የጦርነት ገድል ያለፈ መሆኑን አመልክተዋል።

ድሉ ኢትዮጵያዊያን የሀገርን  ህልውና አደጋ ላይ ለመጣልና ለመውረር የመጣውን ወራሪ ኃይል በተባበረ ክንድ በማሸነፍ  ጀግንነታቸውን ለዓለም ያሳዩበት የአንድነታቸው መገለጫ ነው ብለዋል።

ወጣቱ ትውልድ ከአባቶቹ ጀግንነት በመማር በማንም ሳይታለል ለሀገሩ ህልውና ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የዓድዋ ድል ከጠላት ጋር የሚስተካከልና የሚገዳደር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ባይኖርም ሀገር በመነካቱ ኢትዮጵያዊን ከዳር እስከ ዳር በአንድነት፣ በሀገር ፍቅር ወኔ፣ በእልህና በአልበገርም ባይነት ''ሆ!''ብለው በከፈሉት መስዕዋትነት የተገኘ ድል መሆኑን የገለጹት ደግሞ በጂንካ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር መሪሁን ማዴቦ ናቸው ።

''የዓድዋ ድል በወቅቱ በባርነት አገዛዝ ስር ለነበሩ ለጥቁር ህዝቦች ቅኝ ገዢዎችን በመዋጋት ድል ማድረግ እንደሚቻል ያሳየንበት ተምሳሌትና ደማቅ ታሪካችን ነው'' ብለዋል ።

በዓሉ ሲከበር የስነ ልቦና ግንባታን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ፤ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ የሀገር ፍቅርና ኩሩ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን የሚያሳዩ ተግባራት በማከናወን ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ እይታዎች መሸርሸር የጀመረውን የአንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል ።

በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል ኃላፊና የታሪክ መምህር ሃይማኖት ዓለማየሁ በበኩላቸው''የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በመራር ትግል የገነቡት ትልቅ ሐውልት ነው'' ብለዋል።

የዓድዋ ድል የእኛ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ የጭቁን ጥቁር ህዝቦች ድል መሆኑን አመልክተዋል።

ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት የሆነው የዓድዋ ድል፤ በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ የጥንካሬ መንፈስ  እንደሆናቸው ተናግረዋል።

ወቅቱ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የውስጥ ጉዳዮች መግባባት የተሳናቸው ጊዜ እንደነበርም የታሪክ መምህሩ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን በውስጥ ጉዳይ ላይ መነጋገር የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው ብለው ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው በአንድነት በጠላት ኃይል ላይ በመትመም ሀገራቸውን ማስከበር ችለዋል ብለዋል።

የአባቶቻችን የውስጥ ጉዳዮቻችን ተነጋግሮ የመፍታት ልምድና እሴት ለአሁን ዘመን ትውልድ አስተማሪ መሆኑንም ምሁሩ ገልጸዋል።

የቀደምት አባቶች ጀግንነት፣ ቆራጥነትና አልበገርም ባይነት ሚስጥር አንዱ የሌላውን ድካም መሸፈኑና የዳበረ የመደጋገፍ ባህል መሆኑንም አመላክተዋል።

''አሁን ላይ ሀገራችን የገባችበት የተለያዩ ችግሮችና ከፋፋይ ሀሳቦች በዘመናዊ ባርነት ዳግም አፍሪካን ለመቀራመት የሚቋምጡ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት የወለዱት መሆኑን በመገንዘብ ይበልጥ አንድነታችንን ማጠናከርና ታሪክን ማስቀጠል በሚገባን ጊዜ ላይ ነን'' ብለዋል።

የአድዋ ድል 126ኛ በዓል ነገ በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም