የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡሩንዲ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን ዛሬ ሐዋሳ ላይ ያደርጋል

70
አዲስ አበባ ነሀሴ 27/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን ዛሬ በሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋል። የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ በካሜሮን አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በሚካሄደው የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በመጪው ሳምንት የሚካሄዱ ይሆናሉ። በዚህም ከጋና፣ ሴራሊዮንና ኬኒያ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጳጉሜ 4 ቀን የማጣሪያ ጨዋታውን ከሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል። ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ብሔራዊ ቡድኑ ለወሳኙ የማጣሪያ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ዛሬ ከቀኑ በ10:00 ሰዓት ከቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። በአሰልጣኝ አብርሃም መብሃራቱ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ያለፉትን 25 ቀናት በሀዋሳ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። 24 የልዑካን ቡድን አባላትን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ትናንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን አመሻሹ ላይ ደግሞ ወደ ሐዋሳ ማቅናቱም ታውቋል። በዚህም የወዳጅነት ጨዋታው ዛሬ በ10:00 ሰዓት ላይ በሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ኢንተርናሽናል ዳኞችም የሚመሩት ይሆናል። የኢትዮጵያና የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ህዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም በሴካፋ ውድድር ላይ ሲሆን ጨዋታው በቡሩንዲ 4-1 አሸናፊነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም