የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የድሬዳዋ አስተዳደር

191

ድሬዳዋ/ የካቲት 21/2014 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡን በማጠናከር የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ዛሬ ለብዙሃን መገናኛ ተቋማት መሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ የተዋቀረው የድሬዳዋ አስተዳደር የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡

በተለይ ለአመታት ነዋሪው ከአገልግሎት  አሰጣጥና ከልማት ጋር ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ትርጉም ያለው ምላሽ ለመስጠት የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦች በማካሄድ  የጀመራቸው ስራዎች አበረታች ውጤት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በተለይ አገራዊ ለውጡን ለማጠናከር የህዝብ ጥያቄዎችን በጥናት ለመፍታት በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የተጀመሩ ተግባራትን በማስፋት  ህዝብ በብዛት በሚገለገልባቸው ሌሎች ሶስት ተቋማት ላይ ተመሣሣይ ማሻሻያዎች ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል" ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር የተቀየሱ የዘጠና ቀናት ዕቅዶችን ማስፈጸምና መፈጸም ባቃታቸው ከካቢኔ አባላት ጀምሮ  እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የማሸጋሸግ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

እርምጃው የተወሰደው ከሥራ አፈጻጸም ማነስ፣ ሥራና ባለሙያዎችን አቀናጅቶ መምራት ያልቻሉና የሥነ- ምግባር ችግር የፈጠሩ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"ህዝብን ያማረሩና ለከፋ ሮሮ የዳረጉት አመራሮችን ከደረጃ በማውረድ ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ተደርጓል፤ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ያሉ አሉ" ሲሉም አክለዋል ፡፡

እንደ ከንቲባው ገለጻ አስተዳደሩ አገራዊ ለውጡን በማስቀጠል የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ የጀመራቸውን የለውጥ ተግባራት በቁርጠኝነት ከዳር ለማድረስ ይተጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም