ዞኑ በባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ

61

የካቲት 21/2014 (ኢዜአ) የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳደር በምስራቅ ባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለሁለተኛ ጊዜ ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።

የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀጂ  የተመራ ቡድን በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ዛሬ ተገኝቶ ድጋፉን ለዞኑ አስተዳደርና አባገዳዎች አስረክቧል።

 "የባሌ ህዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በድርቅ ጉዳት ሲደርስበት አለንልህ ለማለትና አብሮነታችንን ለማሳየት ድጋፉን አድርገናል" ብለዋል፡፡

ድጋፉ የኢትዮጵያዊያን የመደጋገፍና በችግር ጊዜ አብሮ የመሆን እሳቤ አንዱ ማሳያ እንደሆነ አቶ አህመድ ገልጸው ችግሩ እስኪቃለል ድረስ የተጀመረው ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዞኑ ለሁለተኛ ጊዜ ለድርቅ ተጎጂዎች ያደረገው ድጋፍ 3ሺህ 10 ኩንታል መሆኑን ጠቁመው  በመጀመሪያ  ዙር 1ሺህ 94 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ በሁለት ዙር የተደረገው የምግብ እህል ድጋፍ 10 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው ነው።

የምስራቅ ባሌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ኢስማኤል በበኩላቸው በዞኑ ለረጅም ወራት የክረምት ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመጣሉ  በአምስት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርብቶ አደሮች ጨምሮ እንስሳቶች ለድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ አርሲ ዞን ህዝብ ያደረገው ድጋፍ ችግሩ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል እየተደረገ ያለውን የመከላከል ስራ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል።

የዞኑ የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሀረግነሽ አለሜ በበኩላቸው "በዞኑ 400 ሺህ የሚጠጉ አርብቶ አደሮች ለድርቁ ተጋላጭ ሆነዋል" ብለዋል፡፡

በድርቅ ምክንያት በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በመደበኛ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም ችግሩ ሰፊ በመሆኑ ከመላው ህዝብና ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም