በአዳማ ከተማ ከ14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ገብተዋል-ጽህፈት ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ ከ14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ገብተዋል-ጽህፈት ቤቱ

አዳማ የካቲት 21/2014/ኢዜአ/ባለፉት ስድስት ወራት ከ14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውን የአዳማ ከተማ የኢንዱስትሪና ኢንቨሰትመንት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በተመሳሳይ ከ923 ሚሊዮን ብር በላይ ከፒታል ያስመዘገቡ አርሶ አደሮች የኢንቨስትመንት ፍቃድ አገኝተው በተለያዩ የልማት አማራጮች ላይ መሰማራታቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጻል።
በዘርፉ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
የአዳማ ከተማ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቱራ ግዛው እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ ከ14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ አግኝተው ወደ ስራ ገብተዋል።
የኢንቨስትመንት ፍቃድ አግኝተው ወደ ስራ የገቡ ባለሃብቶች በተሰማሩባቸው የልማት ዘርፎች ከ44 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ አድል የሚፈጥሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከ923 ሚሊዮን ብር በላይ ከፒታል ያስመዘገቡ አርሶ አደሮች የኢንቨስትመንት ፍቃድ አገኝተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ በአምስት ማህበራት የተደራጁና ከ800 በላይ አባላት ያሏቸው መሆኑን የገለጹት ሃላፊው በአብዛኛው ወደ ኢንቨስትመንት የተሻገሩ አርሶ አደሮች በራሳቸው መሬት ላይ የሚያለሙ መሆኑን አመልክተዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው "ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ በማድረግ ለባለሃብቱና ለአርሶ አደሩ በወቅቱ መሬትና የይዞታ መረጋገጫ ካርታ አስረክበን ወደ ስራ እንዲገቡ አድርገናል" ብለዋል።
ወደ አንቨስትመንት ለተሸጋገሩ አርሶ አደሮች እንዲሁም ለባለሃብቶች ከ85 ሄክታር በላይ መሬት መተላለፉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
"አልሚ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ወደ ስራ እንዳይገቡ እቅንፋት ሊሆኑ ከሚችሉት መካከል የመሬትና የመሰረተ ልማት አውታሮች ችግሮችን ከወዲሁ ለመቅረፍ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመዘርጋት እየሰራን ነው" ሲሉም ከንቲባው አክለዋል።
ከመሬት አስተዳደር፣ ከኢንዱስትሪና እንቨስትመንት ሴክተሮች የተዋቀረ አደረጃጀት በመፍጠር የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለባለሃብቶች እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
የመሰረተ ልማት እጥረትና ከባንክ ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ከክልሉ መንግስትና ከባለደርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በባለሀብቶች ዘንድ ከመንግስት ጋር በገቡት ውል መሰረት መሬቱን ለወሰዱት ዓላማ ከማልማት ይልቅ በአቋራጭ ለመበልፀግ ሌላ አገልግሎቶችና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ የመስጠት ችግር እንደሚስተዋል የጠቀሱት ከንቲባው በመሰል ድርጊት የተሳተፉ ባለሀብቶች በጥናት ተለይተው እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ቃቻ ተሊላ በበኩላቸው ከ36ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ከግንባር ቀደም አርሶ አደርነት ወደ ኢንቬስትመንት መሻገራቸውን ገልጠዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ለሆቴልና ለገበያ ማእከል ግንባታ የሚሆን ቦታ አስረክቦናል ያሉት አርሶ አደር ቃቻ ከባንክ በቂ የብድር አገልግሎት እንድናገኝ ጭምር ከኛ ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።