ቀጥታ፡

በብሔራዊ ምክክሩ የአድዋ የአንድነት ልኬት የሚታይበት ሊሆን ይገባል

የካቲት 21/2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ምክክሩ የአድዋን ድል የጥበብና አንድነት ልኬት የሚያሳዩበት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ 126ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ዛሬ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

ለፓናል ውይይቱ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ዮናስ አሽኔ፤ የአድዋን ድል ከአሁኑ ትውልድ ጋር አያይዘው ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም፤  አድዋ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያን ሪፐብሊክ መሰረት እንደገና ያደሱበት እንደሆነና የጥቁር ህዝቦች መመኪያ መሆኑን ተናግረዋል።

የአድዋ ድል የመበታተን ሳይሆን የመደመርና የአንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸው፤ ድሉ ከሌላው ዓለምና ከአፍሪካ ጥቁር ህዝብ የነጻነት ንቅናቄ ውስጥ የሚካተት ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር የአድዋ ድል የአንድነትን ልኬት በሚያሳይ መልኩ መካሄድና መጠናቀቅ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር ዶክተር ደቻሳ አበበ በበኩላቸው "አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት" በሚል ጽሑፍ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያውያን በአድዋ ድል ዓለምን ያስደነቀ ድል ያገኙባቸውን ምክንያቶች በዘረዘሩበት ጽሑፋቸው አሁን ያለው ትውልድ ከአድዋ መማር ያለበትን ነጥቦች ጠቅሰዋል።

የቁርጠኝነትና የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና፣ አንድነትና ትብብር፣ የአመራር ጥበብና በአሸናፊነት እውቅና ማግኘት ይሄ ትውልድ ከአድዋ የሚወርሰው ነው ብለዋል።

የፓናል ውይይት ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የአሁኑ ትውልድ በአድዋ ላይ የተገኘውን ድል እንደ መነሻ በመውሰድ በምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል።  

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል የጥቁሮችና የነጮች እኩልነትን ያስተማረ ክስተት ነው ብለዋል።

ከአድዋ መልካም እሴቶችን በመውሰድ አገሪቱ አሁን ላለችበት ችግር መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን 1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በአንድነትና በጥበብ ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ድል በማድረግ ለጥቁሮች ነጻነት የሆነውን አኩሪ ታሪክ አስመዘገቡ።

የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ የነጻነት ጮራ የሆነው የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 በድምቀት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም