የሙስና ወንጀል ምርመራ ክስ የተመለከተ ረቂቅ የሥልጠና ሠነድ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የሙስና ወንጀል ምርመራ ክስ የተመለከተ ረቂቅ የሥልጠና ሠነድ ተዘጋጀ

የካቲት 21/2014 (ኢዜአ) የፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ምርመራ ክስ የተመለከተ ረቂቅ የሥልጠና ሠነድ አዘጋጀ።
ኮሚሽኑ የተዘጋጀውን ረቂቅ የሥልጠና ሠነድ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወደ አጦ የሥልጠና ሰነዱን ጥናት ላይ ተመሥርቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለአንድ ዓመት ያክል ሲዘጋጅ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ሠነዱ ኮሚሽኑ መርማሪዎችና አቃቤ ሕጎች በሙስና ወንጀል ላይ ያላቸውን የምርመራና የክስ አቀራረብ ሂደት ለመገንባት የነደፈው ፕሮጀክት አካል መሆኑን ተናግረዋል።
የሥልጠና ሰነዱ ሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር፣ የሙስና ወንጀልን ለመዋጋትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የውይይቱ ተሳታፊ የሕግ ባለሙያ አቶ እውነቴ አለነ፤ የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ሂደት ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።
ሙስናን ወንጀል ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ያላቸውን መርማሪ ፖሊሶችና አቃቢያን ሕጎች እውቀት ለማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁመዋል።
ያም ሆኖ በረቂቅ ሰነዱ ሰልጣኞች በሙስና ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑና የማይሆኑ አካላትን ለመለየት የሚያስችሉ ግልጽ ሃሳቦች ሊካተትበት እንደሚገባ አስረድተዋል።
ሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚመጡ ጥቆማዎችና መረጃዎችንን በምን መልኩ ማስተናገድ እንደሚገባ በሰነዱ ላይ በዝርዝር ቢያካትት የሚል ምከረ ሃሳብም አቅርበዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አስማማው አዳነም በዓለም አቀፍ ሥምምነቶች የተመለከቱ የሙስና ወንጀሎች ምንድን ናቸው? የሚሉት ጉዳዮች ቢካተቱ መካም ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ በረቂቅ ሞጁሉ ሊካተቱ የሚገባቸው በርካታ ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ሠነድ አስፈላጊው ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል።