የአድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን መሰረት የጣለ ልዩ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ ለቀጣይ ትውልድ ማስተማር ይገባል

79

የካቲት 21 ቀን 2014(ኢዜአ) የአድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን መሰረት የጣለ ልዩ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተማር በተለያዩ ኩነቶች መዘከር እንደሚገባ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።

“አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን 126ኛው የአድዋ የድል በዓል አስመልክቶ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ዐውደ ርዕይ ተከፍቷል።

የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም የተገኘው የአድዋ ድል ኢትዮጵያ የጣሊያንን ቅኝ ገዥ ጦር ያሸነፈችበት ቢሆንም በሰው ልጆች ታሪካዊ ሁነቱ ግን ከሌሎች ዐውደ ውጊያዎች የተለያየ አንድምታ ይሰጠዋል።

የታሪክ ምሁራንም አድዋ የምዕራቡ ዓለም በሰው ዘር ላይ ያራመዱትን የተዛባ እሳቤ የለወጠ፤ ለኢትዮጵያዊያን ኩራትና ክብር ያጎናጸፈና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያጎላ አጋጣሚ መሆኑን ይገልጻሉ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሕያው ታሪክነቱ ባሻገር የጥቁር ህዝቦች አሸናፊነት መገለጫ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ለሚማቅቁ አፍሪካዊያን የነጻነት ተስፋ የፈነጠቀ እንዲሁም አፍሪካዊያን እንዲሰባሰቡ ላስቻለው የፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የአድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት የጣለ ልዩ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ ለቀጣይ ትውልድ ማስተማር ይገባል ብለዋል። 

የአድዋ ድል ታሪክ በዓለም ከሚታወቁ ዋና ዋና ጦርነቶች ልዩ ሥፍራ የሚሰጠውና ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ያለው ፋይዳም የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ አልፎ ለፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ መሰረት የሆነውን የአድዋ ድል መዘከር ለቀጣይ ትውልድ ታሪክ ማስተማር ስለሚያስችል የተለያዩ ሁነቶችን በመፍጠር መዘከር ያስፈልጋል ብለዋል።

በዘንድሮው ክብረ በዓል በፎቶና ሥዕል አውደ ርዕይ የተዘጋጀውም የአድዋን ታሪክ ከፍታ ለተከታዩ ትውልድ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

የዐውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች የአድዋ ድልን ታሪካዊ ቱርፋቶች እንዲገነዘቡ ዕድል ይፈጠራልም ነው ያሉት።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፊታችን ረቡዕ ለሦስት ቀናት በሚቆየው ዐውደ ርዕይ ልዩ ልዩ መዛግብት፣ ፎቶግራፎችና ሥዕላት ይቀርቡበታል።

ከዚህ በተጨማሪ "አድዋና ንባብ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የንባብ ሳምንት በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የሚከወን ሲሆን አድዋ ነክ ውይይቶች እንዲሁም የታዳጊዎች የጥያቄና መልስ ውድድሮች ይካሄዳሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም