ክረምት እየተጠበቀ የሚካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በቋሚነት የሚከናወንበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ክረምት እየተጠበቀ የሚካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በቋሚነት የሚከናወንበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ ነሀሴ 27/2010 በአሁኑ ወቅት ክረምት እየተጠበቀ የሚካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በቋሚነት የሚከናወንበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖሊስ አባለትና የደንብ ማስከበር አባላት ገለጹ። ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮችን ከማቃለል ባሻገር በዜጎች መካከል መተሳሰብን ሊፈጥር የሚችለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በቤት እድሳት ሲሳተፉ ካገኘናቸው መካከል ምክትል ሳጂን ሄኖክ ፈይሳ እንደገለፁት በተለይ በዘንድሮ ክረምት የተጀመረው የአረጋዊያንና የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ተግባር የሚያስደስት ነው። የቤት እድሳቱን ጨምሮ በተለያየ መልክ የሚተገበረው የበጎ ፍቃድ ስራ የክረምት ወራት ብቻ ሳይሆን የዘወትር ተግባር ሆኖ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። ረዳት ሳጅን አወል ቡሬ በበኩላቸው ፖሊስ ወንጀልን በመከላከልና የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ተግባሩ የህዝቡን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች ከማንም በላይ በቅርበት ይረዳል። በመሆኑም የአረጋዊያንና የአቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ በሚደረገው ተግባር የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጾ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የክረምት ብቻ ሳይሆን የሁል ጊዜ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል። የደንብ ማስከበር ባለሙያዋ ወይዘሪት ፈቲያ ከድር ደግሞ ከዚህ በፊት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሳትፈው እንደማያወቁ ገልፀው በአሁኑ ወቅት በተጀመረው እንቅስቃሴ ሰዓት በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም የበጎ ፍቃድ ተግባሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ህብረተሰብ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል ብላለች። ሌለኛዋ የደንብ ማሰከበር ባለሞያ ዝይን ጌታ ከበጎ አድራጎት በተጓዳኝ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ ተግባርና ችግሮችን ለይቶ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ በኩል በትኩረት የሚሰሩ መሆኑን ገልፀዋል። "ሰርተው መብላት የማይችሉ አቅመ ደካማ ሰዎችን ሁሉም ሰው ባለው ሙያ ማገልገል ይገባል" ያሉት ደግሞ በአናፂነት ሙያ የተሰማሩት አቶ መርጊያ ቀርቀባ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። በተሰማሩበት ሙያ አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በበጎ አድራጎት ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ ከተማ በእድሜ የገፉና አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን መኖሪያ ቤቶች ለማደስ የታቀደውን መርሃ-ግብር በይፋ ከከፈቱበት ቀን ጀምሮ በርካታ የከተማው ህዝብ በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ብዙዎች ከቤት እድሳት ባሻገር ደጋፊ ለሌላቸው ህፃናት የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስ እና አልባሳት ድጋፍ በማድረግ ላይም ይገኛሉ።