ቀጥታ፡

ማህበራዊ እሴቶቻችንን በአግባቡ አለመጠቀማችን ሀገሪቱን ለችግር እየዳረጋት ነው

የካቲት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ማህበራዊ እሴቶቻችንን በአግባቡ አለመጠቀማችን ሀገሪቱን ለችግር እየዳረጋት ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ገለጹ።

‘ማህበራዊ ሀብቶቻችንና የምሁራን ሚና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ’ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልጋታል።

የሚፈለገው ሰላም ሊመጣ የሚችለው በእውነትና በፍትህ ላይ በመመስረት እንደሆነ ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ አገሪቱ ያላትን ማህበራዊ እሴት በመጤ ባህል ሳይበረዝ በአግባቡ መጠቀም እንዳለባት ጠቁመዋል።

በአሁኑ ሰዓት የማህበረሰብ እሴቶችን በመሸርሸር ሰላምን ለማደፍረስ የሚሰሩ ሃይሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ማንነትን በአግባቡ በመያዝ ለመጤ ባህልና አስተሳሰብ አለመገዛት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

May be an image of 5 people, people sitting, people standing and indoor

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ያጋጥሙ የነበሩ አለመግባባትና ግጭቶች በማህበራዊ እሴቶች ይፈቱ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁንም ሰላም ለማስፈን የማህበረሰቡን የዳበረ እሴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማህበራዊ እሴቶች በመዘንጋታቸውና ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ትናንሽ ችግሮች ትላልቅ ዋጋ እያስከፈሉ እንደሆነ ገልጸው፤ እሴቶቹን ማጠናከርና ስራ ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል።

ይህን ለማሳካት የምሁራን ሚና ወሳኝ ነዉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የማህበረሰብ ማገር የሆኑት መተሳሰብና መተማመንን ለመፍጠር በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መጤ ባህሎች አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ መከላከል ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከመንግስትና ከግል ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራንን ጨምሮ የሐይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም