ቀጥታ፡

በቄለምና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በሌሎች አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ነው

የካቲት 21 2014(ኢዜአ) በቄለምና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም  አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው ሌሎች አካባቢዎች የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች አርሶ አደሮችንና ሌሎች ሰላማዊ ወገኖችን ጭምር በመግደል፣ በመዝረፍና በማገት አሸባሪው ሸኔ በህዝብ ላይ የከፋ ችግር እያደረሰ ይገኛል።

በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑን ለማጥፋት ከህዝብና የተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኃይሌ ጉርሜሳ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሃላፊው እንዳሉት በቄለምና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም ሌሎች አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።

በዚህም የሽብር ቡድኑ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰው በጸጥታ ሃይሉ እየተወሰደ ያለው የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች አሸባሪው ሸኔ የፀጥታ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሌ፤ የጸጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት እየተወሰደ ባለው እርምጃ በአንዳንድ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋና ምዕራብ ሸዋ አካባቢም አሸባሪው ሸኔ በሰዎች ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል መፈፀሙን አስታውሰው በአሸባሪው ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል።

"በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ እንዲሁም በወለጋ ዞኖች የሸኔ የሽብር ቡድን እየተደመሰሰ ነው" ያሉት አቶ ኃይሌ፤ በቄለም ወለጋ አካባቢ በሁለት ወረዳዎች በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ አካባቢው ከሽብር ቡድኑ ነጻ መሆኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ ጉጂ አካባቢም በአሸባሪው ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዶበት ከሽብር ቡድኑ አካባቢው ነጻ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሀገር መከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚኒሻ  እና ህዝቡ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም