የሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ በሙያዋ በመደገፍ የድርሻዋን እንደምትወጣ አርቲስት ዓለም ፀሃይ ወዳጆ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
የሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ በሙያዋ በመደገፍ የድርሻዋን እንደምትወጣ አርቲስት ዓለም ፀሃይ ወዳጆ ገለጸች
ባህርዳር ነሀሴ 27/2010 በሀገሪቱ የተጀመረው ህዝቡን ያሳተፈ የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማስተባበር የድርሻዋን እንደምትወጣ አርቲስት ዓለም ፀሃይ ወዳጆ ገለጸች። አርቲስት ዓለም ፀሃይና ባልደረቦቿ ትናንት ባህር ዳር ሲገቡ በቤተሰቦቻቸውና በከተማዋ ነዋሪዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በዚህ ወቅት አርቲስቷ ለጋዜጠኞች እንዳለችው በስደት ዓለም ውስጥ ሰርቶ ማደር ቢቻልም የሚወዱትን ሀገርና የራስ የሆነን ህዝብ ትቶ መኖር ከባድ ነው። ላለፉት 27 ዓመታት በሀገር ውስጥ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ቆይታዋን በአሜሪካ እንዳደረገች የተናገረችው አርቲስቷ "ኪነ-ጥበብን በሰው ሀገር በራስ ቋንቋን እንደፈለጉ መከወን ባይቻልም ለሀገሬ በምችለው አቅም ስደክም ቆይቻለሁ" ብላለች። አሁን ያለው የሀገሪቱ ነባራዊ የመንግስት ስርዓት ሁሉንም ዜጋ እያሳተፈ በመሆኑ የለውጡን እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ እንደ አንድ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ የራሷን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡ ለዚህም በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የኪ-ነጥበብ ሰዎችን ማስተሳሰር የሚችል ተቋም ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰች እንደሆነም ጠቁማለች የተጀመረው ሀገራዊ የፍቅር ፣አንድነትና የነጻነት አየር በብዙዎች መስዋትነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ይህንን በመጠበቅ ህዝቡ የለውጡ አካል እንዲሆን አርቲስት ዓለም ፀሃይ ወዳጆ መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡ በአሜሪካን የአዲስ ድምጽ ራዲዮ ጋዜጠኛ አበበ በለው በበኩሉ ከ17 ዓመት በፊት በሌለበት ወንጀለኛ ተብሎ 17 ዓመት አስር ተፈርዶበት የሚወዳት ሀገሩን ርቆ ለመኖር እንደተገደደ ተናግሯል። " አሁን መንግሰት ባደረገው የይቅርታና የተባብረን ሀገራችን እንገንባ መንፈስ የምወዳትን ሀገሬንና ህዝቤን በአካል ለማየት አብቀቶኛል" ብሏል፡፡ ጋዜጠኛ አበበ በሙያው በሀገር ውስጥ ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት አንድነትንና ፍቅርን የሚያዳብሩ ስራዎችን ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጿል። በሀገር ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚል ሃሳብ የሚያነሳ ሁሉ እንደወንጀለኛ ይታይ የነበረው አሁን ተቀይሯል፡፡ " በአገር ጉዳይ ላይ የሚመስለውን ሃሳብ መናገር ለአገር እድገት እንደግብዓት ይቆጠራል ወደ ሚል የመንግስት ስርዓት መሸጋገር መቻሉ በውጪ የሚኖረው ዲያስፖራ ለአገሩ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ እንዲዘጋጅ አደርጎታል" ብሏል ጋዜጠኛ አበበ፡፡