ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ከብክለት ነፃ የሆነ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

የካቲት 20/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ከብክለት ነፃ የሆነ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የተቋሙ አመራሮች በምስራቅ ኢትዮጵያ የተለያዩ የውሃና ኢነርጂ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የባዮጋዝ ኢነርጂ ልማት ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ፤ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከብክለት ነፃ የሆነ የኃይል አቅርቦት ለማስፋፋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በ2023 ዓ.ም 63 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆን እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከገጠር የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሶላር፣ በባዮጋዝ እና ኤል ፒጂ ጋዝ 35 በመቶውን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

ጭስ አልባ የሆኑ የማብሰያ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እንደ ባዮጋዝ ያሉ የሃይል አማራጮች በስፋት ስራ ላይ እየዋሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ አማራጭን ለማስፋት የግንዛቤ ማስፋት ስራ አስፈላጊ በመሆኑ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ሊያግዙ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ በቀላሉ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎች ቢኖርም ትኩረት በመነፈጉ ውጤቱ እምብዛም ሆኗል ነው ያሉት።

የባዩ ጋዝ ቴክኖሎጂን ከሀረሪ ክልል፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ውጪ ተግባራዊ በማድረግ በዚህ ዓመት ከ500 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የባዩ ጋዝ ቴክኖሎጂን እየተጠቀሙ ያሉ ግለሰቦችም በአገልግሎቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም