ቀጥታ፡

የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል ውጤት እያመጣ ነው

የካቲት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል ውጤት እያመጣ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሚኒስቴሩ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ዮሐንስ አመነ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር ወጣቶች በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ማገልገላቸው ከስራው ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እያጠናከር ይገኛል።

ከ21 ሺህ በላይ ወጣቶች በግብርና ስራዎች፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት፣ በትራንስፖርት ስምሪትና በሌሎችም መስኮች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የተለያዩ ክልሎች የሰላም ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪዎችም ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልገሎት በሰላም ግንባታና በህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጠናከር ረገድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የካቢኔ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፒተር ኦይ፤ ክልሉ በሰላም ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጸጥታ ጥበቃ በተጨማሪ መከካበርና መቻቻል እንዲኖር የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ የሚገኙት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች የህዝብ ለህዝብ ግንኝነትን ለማጠናከር አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ፤ በክልሉ 3 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ስራ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀመሪው ዙር 1 ሺህ 200 ወጣቶች በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንድ ዓመት ሲሳተፉ ቆይተው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ሲዳማ ክልል የመጡ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶችም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሰማርተው ውጤት እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል።

በተለያዩ ችግሮች መርሃ ግብሩ እየተፈተነ ቢሆንም ፈተናዎችን በማለፍ ምክንያታዊ ማህበረሰብ ለመፍጠርና የ2063ቱን የልማት ግብ ለማሳካት እንሰራለን ብለዋል የበጎ ፈቃድ አስተባባሪው ዶክተር ዮሐንስ አመነ።

በወጣቶቹ የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ ብሔራዊ አገልግሎት ለማሳደግ ግብ መቀመጡንም ጠቁመዋል።

በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች፣ በክልሎች የታችኛው መዋቅር በባለቤትነት አለመምራት፣ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዘንድ የጠባቂነት ስሜት መኖር መርኃ ግብሩን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሄድ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም