ቀጥታ፡

የዐድዋ ድል በዓልን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል

የካቲት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የካቲት 23 የሚከበረውን የዘንድሮ የዐድዋ ድል በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

የዘንድሮ የዐድዋ ድል በዓል “ዐድዋን ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን በፌዴራል ደረጃ በድምቀት ለማክበር የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የበዓሉ ባለቤት ሆኖ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነው ያስታወቁት።

በዓሉን በደመቀ ሁኔታ በመላ አገሪቱ ለማክበር የሰላም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበር፣የቅርስ ባለሥልጣን፣መከላከያ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት የተካተቱበት ዐቢይ ኮሚቴ፣ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን የአገር ውስጥ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲምፖዚየም እንዲሁም የውጭ ዲፕሎማቶችን እና ዲያስፖራውን የሚያሳትፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሲምፖዚየም እንደሚኖርም አመልክተዋል።

ኤግዚቢሽኖች እና የስፖርት ኩነቶች መዘጋጀታቸውንም ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ የፈረስ ትርዒቶችም የበዓሉ ድምቀቶች እንደሚሆኑ ተናግረዋል።በዓሉ በክልል ደረጃም ተመሳሳይ ዝግጅት ተደርጎ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ መስተዳድር እና ኦሮሚያ ክልል ጋርም አዲስ አበባ የሚከበር በመሆኑ አንድ ላይ በመቀናጀት ለማክበር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዐድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ትልቅ በታሪክ የተመዘገበ ድል ነው ያሉት አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ የዐድዋ ጦርነት በተደረገበት ወቅት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ወደ አፍሪካ ተስማምተው የዘመቱበት እና አብዛኛዎቹን የአፍሪካን አገሮች በቀላሉ መቆጣጠር የቻሉበት ቢሆንም በኢትዮጵያ ያልጠበቁትን ሽንፈት ተከናንበው የተመለሱበት መሆኑን አስታውሰዋል።

የተገኘው ድል በወቅቱ ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያ ባትታጠቅም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የዳበሩ የውጊያ ስልቶች እና በሌሎች ዘንድ ያልተለመደውን የፈረስ ውጊያ ስልቶችን በመጠቀም የተገኘ ትልቅ ድል መሆኑን ጠቁመዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ልምድ እና ችሎታ በመጠቀም በጋራ እና በአንድነት ቆመው ጦርነቱን ማሸነፍ ችለዋል ብለዋል።

አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንደሚሉት ወጣቱ ከዐድዋ ድል አገር ወዳድነትን እና ለአገር ነጻነት መቆምን መማር አለበት።

ዐድዋ በትልቅ መሥዋዕትነት በርካታ ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎችን ጨምሮ ተሠውተውበት የተገኘ ድል መሆኑን መረዳት ይኖርበታል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ከዐድዋ በመማር ወጣቱ በቆራጥነት አገሩን መጠበቅ እና መከላከል እንዳለበት ጠቁመው፤ በዓሉን ወጣቱና ሁሉም ሕዝብ በነቂስ በመውጣት እንዲያከብርና ለበዓሉ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽንም እንዲጎበኝ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም