የፖለቲካ ፓርቲዎች የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስራዎችን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስራዎችን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል
ሀዋሳ፤ የካቲት 19/2014 (ኢዜአ)፡በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስራዎችን ማገዝ እንደሚጠቅባቸው የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ አስገነዘቡ።
በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ በሀዋሳ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በሀገሪቱ በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡ ቢሆንም የልማት ስራዎች እየተካናወኑ ነው።
በአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እየደረሰ ያለው የሽብር ተግባርን ለመመከት መንግሥት ከኢትዮጵያውያን ጋር የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል እያካሄደ ያለውን ዘመቻ በድል እየተወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር አንዳንድ ምዕራባውያን ያልተገባ ተጽዕኖዎችን በማድረግ በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ቢጋረጡም፤በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በትብብር የሰሩት ስራ ለተገኘው ድል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
በክልሉ ብለም በሀገሪቱ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አፈ- ጉባኤዋ ጠቅሰው፤የልማት ስራዎቹን በስኬት ለማጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
መንግሥት በክልሉ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ወይዘሮ ፋንታዬ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ስራ ፈጣሪ በመሆን ከስራ ጠባቂነት እንዲላቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎቻቸውን በማስተባበር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጋር በማበር ያልተገባ ተፅዕኖ ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ ታምራት አሰፋ ጠቁመዋል
''የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ጉዳይ ቀልድ አያውቅም'' ያሉት አቶ ታምራት፤ በአንድነት ሆ ብሎ በመነሳት የሀገር ህልውናን ለማስከበርና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ያደረገው ርብርብ ውጤት ማሰገኘቱን ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ እየተከናወኑ ባሉና በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሀገር ላይ በርካታ ተግዳሮት የተደቀኑ ቢሆንም ለችግሮች ባለመንበርከክ ስኬታማ የሆነ ስራ መስራት መቻሉን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ አቶ ለገሰ ላንቃሞ ገልጸዋል።
የታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ ወደ ስራ መግባቱ የሚያስደስት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገራው የምክክር መድረክ ለማካሄድ እየተሰራ ያለው ቅድመ ዝግጅት ስራ እንዳስደሰታቸው የገለጹት አቶ ለገሰ፤ ፓርቲያቸው ለዚህ ስኬት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ተወካይና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ የኋላሸት በቀለ በበኩላቸው በሲዳማ ክልል ያለውን ሰላም በማስቀጠል ክልሉን ለኑሮና ለስራ ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ተግባር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በክልሉ አጎራባች በሆኑ አካባቢዎች አሸባሪው ሸኔ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ ፓርቲዎች በጋራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበው፤ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በህብረት አንድ ሆነው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በክልሉ ስኬታማ እንዲሆን የጋራ ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ አባል ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸው በማስተባበር ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ብልጽግና፣ ህብርና ሲአንን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎችን የያዘ መሆኑ ኢዜአ ዘግቧል።