የሐረሪ ክልል ከምስራቁ የአገሪቱ አካባቢዎች ጋር በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሐረሪ ክልል ከምስራቁ የአገሪቱ አካባቢዎች ጋር በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወነ ነው
የካቲት 19/2014( ኢዜአ) የሐረሪ ክልል ከምስራቁ የአገሪቱ አካባቢዎች ጋር በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በሐረሪ እና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ለተውጣጡ ጋዜጠኞች እያስጎበኘ ይገኛል።
የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ቅርሶችን በሚመለከት መረጃ ተደራሽ በማድረግ ኀብረተሰቡ በቅርሶች እንክብካቤ እና ጥበቃ ላይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ ማስቻል ነው፡፡
በዛሬው እለትም በሐረር ከተማ በመገኘት የሐረር ባህል ማዕከል፣ የጀጎል ግንብ፣ እና ሙዚየሞችን ጎብኝተዋል፡፡
የሐረሪ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወልዳ አብዶሽ በዚህን ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ።
ክልሉ ቅርሶቹን ጠብቆ በማቆየት ረገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ከኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ ክልሎች እና ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በዘርፉ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናቀዋል ነው ያሉት፡፡
ይህም አካባቢዎቹን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች የተቀናጀ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ያግዛል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት እና የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡