ቀጥታ፡

የቻይና ወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያን ልማት መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

ቻይና ቤጂንግ ነሐሴ 27/2010 የቻይና ወጪ እና ገቢ ንግድ (ኤግዚም) ባንክ የኢትዮጵያን ልማት መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። በቻይና አፍሪካ ፎረም ጉባኤ  ለመሳተፍ ቤጂንግ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር ዐቢይ አህመድ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዛሬው እለትም ከቻይናው ኤግዚም ባንክ  ሊቀመንበር ሚስ ሁ ዥዖሎያን ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ  ባንኩ የኢትዮጵያን ልማት ለማፋጠን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጡን  ውይይቱን የተከታተሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገልፀዋል። ባንኩ ከዚህ ቀደምም ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበረው ያስታወሱት ዶክተር ይናገር፤ ወደፊትም ከ45 በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች ብድር እንደሚያቀርብ ነው ያረጋገጡት። በውይይቱ ለወለድና ብድር አከፋፈል ጉዳይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፤ በቀጣይ አብሮ ስለመስራት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም ዶክተር ይናገር አመልክተዋል። የባንኩ ሊቀመንበር ሚስ ሁ ዥዖሎያን  ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት፤ ባንኩ በኢትዮጵያ ወሳኝ የሚባሉ የልማት መስኮች ላይ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ሙሃመድ ጋርም ቤጂንግ ተገናኝተው በአገሮቹ እና በቀጠናው የጋራ ጉዳዮች  ዙሪያ መክረዋል። በተያያዘ ዜና የቻይና አፍሪካ ፎረም ጉባኤ አካል የሆነው የሚንስትሮች ስብሰባ በመካሄድ ላይ ነው። የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ነገ ለሚጀመረው የመሪዎች ጉባኤ የመወያያ አጀንዳዎችን ይቀርጻል። በዚህ ስብሰባ  የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁም ተካፋይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም