ቀጥታ፡

ኢዜአ ብሔራዊ መግባባትና የገጽታ ግንባታን የሚያጎለብቱ መረጃዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው

የካቲት 19/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትና የገጽታ ግንባታን የሚያጎለብቱ መረጃዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች የሚያከብር ሲሆን፤ በዛሬው እለትም ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስና ሌሎች ስራዎችን ለባለድርሻ አካላት አስጎብኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚህን ወቅት የተቋሙን የ80ኛ ዓመት አከባበርና በለውጥ ስራዎች የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል። 

ኢዜአ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባገኘው የሙያ ድጋፍ የተቋሙን ነባር ህንጻ በማደስ ምቹና ማራኪ የስራ አካባቢን መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ይህም የተሻለ የግንባታ አቅም ያላቸው የአገር ውስጥ ተቋማት መኖራቸውን ያመላከት ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ተቋሙ አዲስ ያስገነባው የህጻናት ማቆያ ህንጻ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህም የተቋሙ ሰራተኞች ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡ ተረጋግተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ተቋሙ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሶስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ስቱዲዮዎች፣ ጂም እንዲሁም ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ያካተተ እጅግ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ግንባታ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ስቱዲዎቹን በግብዓት የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑንና በቀጣይ ነሃሴ ወር በሚደረገው የተቋሙ 80ኛ ዓመት ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ላይ የህንጻው ስራ መጀመር ይበሰራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያብራሩት፡፡

ተቋሙ 80ኛ ዓመቱን ሲያከብር በቀጣይ ብሔራዊ መግባባትንና የገጽታ ግንባታ ስራዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሆነም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሳምንት የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም የተቋሙን የ80 ዓመት ጉዞ እንዲሁም የአገር ህልውናን በማስጠበቅ ረገድ ያበረከተውን ሚና የሚቃኝ የፓናል ውይይትና አውደ-ርዕይ እንደሚዘጋጅም ጨምረው  ገልጸዋል። 

ኢዜአ በተለያዩ ክልሎች 36 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ በአገር ውስጥ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም በትግርኛ ቋንቋ የመረጃ ስርጭት እንደሚጀምር ነው ያረጋገጡት፡፡

በተመሳሳይ በእንግሊዘኛና አረብኛ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተደራሽነቱን እንደሚያሰፋ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በ2022 ዓ.ም በዜና አገልግሎት ዘርፍ ቀዳሚና ተመራጭ ተቋም የመሆን ውጥን ይዞ እየሰራ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሰይፈ ደርቤ ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ የቦርድ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ኢዜአ በቀጣይ መረጃዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አግልሎት በ1934 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

ተቋሙ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም