ቀጥታ፡

የአይሻ ሁለት ንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ከ77 በመቶ በላይ ተጠናቀቀ

የካቲት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአይሻ ሁለት ንፋስ ኃይል ፕሮጀክት የኃይል ማመንጨት ሥራ ሊጀምር መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ።
የውሃ ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ኃብታሙ ኢተፋና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሶማሌ ክልል ሺኒሌ ዞን አይሻ ወረዳ እየተገነባ ያለውን የአይሻ ሁለት ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ኃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአይሻ ሁለት ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በመሆኑንም በቅርቡ 40 ሜጋ ዋት ኃይል የሚሆን ኃይል የማመንጨት ሥራ ይጀምራል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ምንም እንኳን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባይካሄድም በቅርቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

በቀጣይም የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ሥራዎችን በስፋት በማካሔድ ኅብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ መሐንዲስ ኢንድሪስ ገዙ በበኩላቸው 120 ሚጋ ዋት የንፋስ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የፕሮጀክቱ ግንባታው ከ77 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ ካሉት 48 ዩኒቶች መካከል የ32ቱ የኤክትሮነካል ሥራ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

እያንዳንዱ ዩኒት 2 ነጥብ 5 ሜጋዋት ኃይል እንደሚያመነጭ ጠቁመው የሰብስቴሽን ግምባታም እንዲሁ 93 በመቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

የሁሉም የሲቪል ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን የመሥመር ዝርጋታ ሥራውም ከብሔራዊ ግሪድ ጋር ተገናኝተዋል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታው በቻይናው ዶንግፈንግ ኢንተርናሽናል ኩባንያ እየተካሔደ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም