ቀጥታ፡

መንግሥት በዲፕሎማሲው መስክ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ምሁራን

ሀዋሳ ፤ የካቲት 19/ 2014(ኢዜአ) መንግስት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ያላትን ተሰሚነት መሰረት በማድረግ በዲፕሎማሲ መስክ ገጽታዋን ለመገንባት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን አመለከቱ።
በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ግንኙነትና አልሙኒ ጉዳዮች ዳይሬክተርና የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ዮሃናን ዮካሞ እንዳሉት፤ የዲፕሎማሲ ስራ ለአንድ ሃገር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መፍጠሪያ ትልቁ መሳሪያ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነት ተጠቅማ የጀመረችውን የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከር እንዳለባት አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ሰሞኑን ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ከመንግስታቸው ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ የዲፕሎማሲ ስራውን ማካታተቸው ወቅቱ የሚጠይቀውና ተገቢነት እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የጀመረችውን ስራ  ስኬታማ እንዲሆን  በሙያው የሰለጠኑና ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች እንደሚያስፈልጉም ነው የጠቆሙት።

እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተሰሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቦባቸዋል።

በቀጣይ በዘርፉ ከዚህ በተሻለ ውጤት ለማምጣት በውጭ ሀገራት የሚመደቡ ዲፕሎማቶች በሙያው የሰለጠኑ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

በጥቂት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዲፕሎማሲ ማዕከላት መገንባታችው መንግሥት ሊሰራ ያሰበውን የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያጠናክርም አመላክተዋል።

ምሁራኑ የሀገር ገጽታን ለመገንባት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ማዕከላቱ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ንጉስ በላይ በበኩላቸው፤ ምዕራባዊያን የተካኑበት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ አሁን አሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካም እየተለመደ መምጣቱን አስረድተዋል።

በመላው ዓለም ኢትዮጵያዊያንን ያነሳሳው የበቃ "no more " ዘመቻ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ ስራዎች መከናወናቸውንና ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

"እንደ ሀገር የዲፕሎማሲ ስራውን ማጠናከር ላይ አቅጣጫ መቀመጡ ተገቢ ቢሆንም ሁሉም ሰው ለሀገሩ ዲፕሎማት ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችለውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ማጠናከር ለስኬት ያግዛል" ነው ያሉት።

ዶክተር ንጉስ እንዳሉት፤ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩበት ቢሆንም በተገቢው ልክ አልተሰራበትም።

በተለይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የዓለምን ትኩረት እየሳበች በመሆኑ  ጊዜውን የሚመጥን የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የምትችል ሀገር ሆና እንድትቀጥል መንግስት በዲፕሎማሲው መስክ ያስቀመጠውን አቅጣጫ በአግባቡ ለመተግበር መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

"አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት እየተገነቡ ነው" ያሉት ዶክተር ንጉስ፤ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች እድሉን በመጠቀም የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት  ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ  ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ቀጣይ የትኩረት መስኮች ብለው ካነሷች አምስት ጉዳዮች መካከል ዲፕሎማሲ አንዱ መሆኑን በወቅቱ ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም