ቀጥታ፡

ሕዝበ ክርስትያኑ በመጪው ዐቢይ ጾም ጥላቻን በማስወገድ ለአገር ሰላምና አንድነት አጥብቆ ሊጸልይ ይገባል

የካቲት 19 2014(ኢዜአ) ሕዝበ ክርስትያኑ በመጪው ዐቢይ ጾም ጥላቻን በማስወገድ ለአገር ሰላምና አንድነት አጥብቆ እንዲጸልይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመጪው ሰኞ የሚጀመረውን የአብይ ጾም አስመልክቶ የእንኳ አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የጾሙ ወቅት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና አንድነት እንዲሰፍን ወደ ፈጣሪ የምንማፀንበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ ህዝበ ክርስቲያኑ በድርቅና በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ካለው በማካፈል ጾሙን ሊያሳልፍ እንደሚገባም ነው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጾሙ ከምግብ የምንከለከልበት ብቻ ሳይሆን ከጥላቻ እና መከፋፈል የምንቆጠብበት፤ የተቸገሩ ወገኖችን የምንደግፍበት ሊሆን ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል ።

በኢትዮጵያ አጋጥመው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ቤተክርስቲያን ጉዳት እንደደረሰባት አስታውሰው፤ በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያኑ ስለአገርና ቤተክርስቲያን አንድንት ፈጣሪውን ሊማጸን ይገባል ነው ያሉት፡፡

''እርስ በእርሳችን ሳንዋደድ ወደ ፈጣሪ መቅረብ አይቻልም''ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ከዚህ አኳያ ጥላቻንና መራራቅን በማስወገድ እርስ በርስ መዋደድና መደጋገፍ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም