የማርና ሰም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 1 ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎዎች ሊሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማርና ሰም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 1 ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎዎች ሊሰራጩ ነው

የካቲት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የማርና ሰም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 1 ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎዎችን ለማሰራጨት እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በግብርና ሚኒስቴር የማርና ሐር ኃብት ዳይሬክተር አብርሃም ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 500 ሺህ ቶን ማርና 50 ሺህ ቶን ሰም ለማምረት የሚያስችል አቅም አላት።
ይሁንና አገሪቱ እስካሁን ማምረት የቻለችው ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ ነው የገለጹት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታና ከአርሶ አደሩ የግብይት ሰንሰለት ጋር ተያይዞ ወደ ውጭ የሚላከው የማር ምርት መጠን መቀነሱንም ነው የተናገሩት።
የዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በስፋት አለመጠቀም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሚመረቱ ቀፎዎች ጥራት መጓደልና የአርሶአደሩ በቂ ክህሎት አለመኖርም ለምርቱ መቀነስ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ያም ሆኖ ምርታማነትን ለመጨመር ቀፎን የማዘመን ሥራና ለአረንጓዴ ልማት የሚተከሉ ችግኞችን ለንቦች ተስማሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ዘመናዊ የሽግግር ቀፎዎች፣ ባለፍሬም ቀፎና ኢትዮ-ርብራብ ቀፎዎች በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በማር ምርት የሰለጠኑ ወጣቶችን ወደ ሥራው እንዲገቡ የማድረግም ተግባር እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በተጓዳኝም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በአማራ ክልል የእናት ንብ ማባዣና የሥልጠና ማዕከል ተገንብተው በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም አስረድተዋል።
በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የማር ምርትን ማግኘት እንደሚቻል የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እምቅ አቅም ያላቸውና ዓመቱን ሙሉ ምርት የሚገኝባቸው ሥፍራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የንብ ምርትን የማቀነባበርና ምርቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከአሥር ዓመት በፊት አባል የሆነችበት የዓለም አቀፉ ንብ አናቢዎች ፌዴሬሽን የገበያ ትስስር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሙያ ልውውጥ እንድታገኝ እገዛ ማድጉን ገልጸዋል።
የ2013 በጀት ዓመት የማር ምርት መጠን 129 ሺህ ቶን ሲሆን የሰም ምርት ደግሞ 6 ነጥብ 3 ሺህ ቶን እንደነበር ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በአገራችን 1 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑ አርሶአደር፣ ከፊል አርብቶ አደር፣ ባለኃብቶችና የከተማ ነዋሪዎች የንብ ኤክስቴንሽን ምርት አናቢዎች ይገኛሉ።