ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የወርቅ ሃብትን ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል እየተሠራ ነው

አሶሳ ፤ የካቲት 18 / 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የወርቅ ሃብት በአግባቡ በማልማት ለኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በምርትና ግብይትን ማዘመን ላይ ያተኮረ ስልጠና በአሶሳ ከተማ  ተሰጥቷል፡፡

የሚኒስቴሩ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ይማም በዚሁ ወቅት፤ ሚኒስቴሩ የሀገሪቱን ማዕድን ለማልማት በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ወርቅ በአሁኑ ወቅት ከቡና ቀጥሉ ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ የሚገኝት ዘርፍ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፤  የወርቅ ሃብት በአግባቡ በማልማት ለኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባህላዊና አነስተኛ ወርቅ አምራቾች ቁጠባን መሠረት በማድረግና  ዘመናዊ ማምረቻ መሣሪያዎችን በመጠቀም ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አቶ መሐመድ ገልጸዋል፡፡

በባህላዊ ምርት የተሰማሩ ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዲጠቀሙ እንዲሁም የግብይት ሂደቱ ህጋዊ አካሄድን ብቻ እንዲከተል እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በዘርፉ የሀገር ውስጥና የውጭ ትላልቅ ኩባንያዎች በስፋት በማስገባት የተፈጥሮ ሃብቶችን በስፋት ለማልማት ጥረት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በእስካሁኑም ሂደት በዘርፉ ኩባንያዎቹ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ናስር መሐመድ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ከአሶሳ ዞን ብቻ ከ10 ኩንታል በላይ ወርቅ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በተጠቀሰው ጊዜ በባህላዊ መንገድ የተመረተ ከ20 ኩንታል በላይ ወርቅ ታቅዶ እንደነበር ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና በካማሽና በመተከል ዞኖች በነበረው   የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርቱን ለማቅረብ ባለመቻሉ  አፈጻጸሙ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በግንዛቤ ማነስ ምርትን ወደ ብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ሲገባ በቤት ውስጥ ማስቀመጥ፣ የቁጠባ ባህል ማነስና የህገ-ወጥ ወርቅ አዘዋዋሪዎች መበራከት በክልሉ የዘርፉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በባህላዊ ወርቅ አመራረት የሚከሰተውን የአፈር መሸርሸርና በእጽዋት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት  ጥረት እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በአሶሳ ዞን የመንጌ ወረዳ ባህላዊ ወርቅ አምራች አቶ አንዋር ሃሚድ  በሰጡት አስተያየት፤ በህገ-ወጥ ደላሎች ማክንያት ዘመናዊ ማምረቻ ማሽኖች በሚፈልጉት ልክ አለማግኘትና ምርትን በሚገባው መጠን ወደ ብሔራዊ ባንክ አለማስገባት ችግር  እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ወደ አነስተኛ የወርቅ አምራች በመሻገርና ህጋዊ ግብይትን በመከተል የተሻለ ውጤት ለማምጣት   እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በአሶሳ፣ ካማሽና መተከል ዞኖች ከሚገኙ 21 ወረዳዎች መካከል በአብዛኞቹ የደለልና የጽንሰ ወርቅ ሃብት እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ኢትዮጵያ በ2013 የበጀት ዓመት ከማዕድን  681 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም