በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ግብረ ኃይል ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ግብረ ኃይል ተቋቋመ
ድሬዳዋ፤ የካቲት 18/2014(ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር የተጎዱ ወገኖችን በተቀናጀ መንገድ የሚደግፍ ግብረ ኃይል አቋቋመ።
ግብረ ኃይሉ በአስተዳደሩ ከንቲባ የሚመራ አብይና 15 ንዑሳን ኮሚቴዎች አሉት፡፡
አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎቹ 21 አባላት ያሏቸው ሲሆኑ፤ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የኃይማኖት፣ የሲቪክ፣ የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የዑጋዝና የአባገዳ ተቋማት መሪዎች እንደተካተቱበት ተገልጿል።
ግብረ ኃይሉ ሲቋቋም የአብይ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የድሬዳዋ አስተዳደርና ነዋሪዎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱን ዜጎች ለመደገፍ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው፡፡
እስካሁንም በአፋር፣ አማራ፣ ሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን በገንዘብ፣ በአልባሳትና በምግብና በጤና ግብዓቶች መደገፉን አስታውሰዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ በተለይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን በተቀናጀ መንገድ ለመደገፍ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
''የገጠሙንን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች በመተባበርና በመደጋገፍ በመሻገር ሀገርን አፅንቶ ማቆም የትናንት፣ የዛሬና የነገም መገለጫችንን ይሆናል'' ብለዋል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ የድሬዳዋ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ፤ አስተዳደሩ ከነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት በጦርነትና በድርቅ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
"ግብረ-ኃይሉ አሁን ላይ በተለይ በድርቅ አደጋ ለተጎዱና አስቸኳይ ደራሽ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ለመደገፍ የተሻለና የተቀናጀ ውጤት ለማምጣት ያስችላል" ብለዋል፡፡
የድጋፉ አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል በተቋቋመበት ሥነ-ሥርዓት የተገኙት የኃይማኖት አባቶች፣ ዑጋዞችና አባገዳዎች የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚከናወኑ ተግባራት ህብረተሰብ አስተባብረው የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡