ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ አገር ለመገንባት ጉልህ ሚና ይኖረዋል

የካቲት 18 2014 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ የምታካሂደው አገራዊ ምክክር ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ አገር ለመገንባት እንደሚያስችላት በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሺትኪንቶንግ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚያስችሉ ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታችና አሳታፊ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች ሲሆን፤ በቅርቡም አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁማለች።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር  ሮበርት ሺትኪንቶንግ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ እንደ ህንድ  አያሌ ቋንቋዎችንና ብዝሃ-ማንነቶችን ያቀፈች አገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ህንድና ኢትዮጵያ ካላቸው ብዝሃ-ማንነት አንጻር ሕብረ ብሔራዊ አንደነታቸውን አስጠብቀው የዘለቁ አገራት መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ አኳያ ሁለቱ አገራት እርስ በእርስ መማማር የሚችሉባቸው አያሌ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመው ኢትዮጵያ ልታካሂድ የወሰነቸው አገራዊ ምክክር መድረክም ብዝሃነቷን አክበራ፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ አገር ለመገንባት እንደሚያስችላት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

አገራዊ የምክክር መድረኮች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕንድ ብዝሃ ማንነት ባላቸው አገሮች አብሮነትን በማጎልበት ለአገር ግንባታ በጎ ሚና እንደሚኖራቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላት ሕንድ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በሚመለከት ባካሄዳቸው ስብስባዎች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር መሞገቷን አውስተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት በኒውዮርክና ጄኔቫ በተደረጉ ስብሰባዎችም ኢትዮጵያ ለውስጣዊ ጉዳዮቿ በራሷ መፍትሔ መስጠት እንደምትችል አቋሟን መግለጿንም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም